የአርሶ አደሩ መራራ ሕይወት በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ።

124

ሰቆጣ: መጋቢት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ጣፈጠ ዘረዮሐንስ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አበርገሌ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ጣፈጠ በግብርና ሥራ አስር ቤተሰብ ያሥተዳድራሉ። አራት ልጆችንም ያስተምራሉ። አንዱን ለዩኒቨርሲቲ አብቅተዋል፤ ኹለቱን ጎጆ እንዲወጡ አድርገው እዛው ጎረቤት ጎጆ ቀልሰውላቸው፣ የሞቀ ኑሮ ነበር የሚመሩት። አርሶ አደሩ “ሰላም አውለኝ” ብለው አርሰው ቤተሰቦቻቸውን ከመምራት ባለፈ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የላቸውም። ሀገር አፍራሹ እና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ግን ለነ አርሶ አደር ጣፈጠ የሰላም ሕይወት እንኳ ቅንጣት ታህል ርህራሄ አልነበረውም፡፡
አኹን ያ እንደስማቸው የጣፈጠ ኑሮአቸው የለም፤ የሞቀ እና የፍቅር ቤተሰብ በአንድ ላይ አይመክርም፤ አይዘክርም፤ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ወረራ ሃብትና ንብረታቸው በመዘረፉና በመውደሙ ቤተሰቡ እግር ወደ መራው እንዲሰደድ ግድ ኾነበት። አቶ ጣፈጠ ያለፈው ሰኔ ነበር ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱት።
አኹን ላይ ቤተሰቦቻቸው በዝቋላ፣ ሰቆጣ እና በወለኽ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ይገኛሉ። ቤተሰቡ በዚኽ ወቅት ችግር በአንድ መጠለያ ጣቢያ እንኳ ማረፍ አላስቻላቸውም፤ አቶ ጣፈጠ አንዷን ታዳጊ ልጃቸውን ይዘው ከባለቤታቸው እና ከሌሎች ልጆቻቸው ተለይተው በወለኽ የመጠለያ ጣቢያ ነው ተጠልለው የሚገኙት።
ልጆቻቸውም ትምሕርታቸውን ካቋረጡ ዓመት አስቆጥረዋል። በጉርብትና ይኖሩ የነበሩ ኹለት ጎጆ የወጡ ልጆቻቸውም ልክ የወላጆቻቸው እጣ ፋንታ ገጥሟቸዋል፡፡
“አንድ ሰኔ የጣለው፣ ሦስት ሰኔ አያነሳውም” እንደሚባለው አቶ ጣፈጠ ባለፈው የምርት ዘመን ማምረት ባለመቻላቸው የቤተሰባቸው ሕይወት በሙሉ በሰው እጅ ወድቋል፡፡
አቶ ጣፈጠ በመጠለያ ጣቢያው አብረው የሚኖሩ ሌሎች ታዳጊዎችን የዕለት ጉርስ ለማብሰል መዳፍ በምታክል የብረት ምጣድ የተጋገረ ቂጣ ማውጣት የዕለት ሥራቸው ከሆነ ሰነባብቷል፤ ለዛውም የሚጋገረው እህል ከተገኘ።
አቶ ጣፈጠ በዚህ የምርት ዘመንም ማምረት ካልቻሉ በቀጣይም ቤተሰባቸው በከፋ ችግር ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
አርሶ አደሩ አኹንም በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ሥር የወደቁ አካባቢዎችን ነጻ በማድረግ ወደ ግብርና ሥራው እንዲመለስ መንግሥት የመንግሥትነት ሚናውን እንዲወጣ ተማጽነዋል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወደ አካባቢው እንደገባ ከ18 በላይ ንጹሃን መጨፍጨፋቸውን አስታውሰዋል። የሚያሳዝነው ደግሞ ሴቶችን ጭምር መግደላቸውን ነው አቶ ጣፈጠ በሐዘን ያነሱት። የሽብር ቡድኑ አስገድዶ መድፈር ፈጽሟል፤ ገንዘብ ዘርፏል፤ የገበሬውን ቤት እና የግብርና መሳሪያ ሳይቀር አውድሟል ብለዋል፡፡
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደደር በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ዜጎች ባለፉት ወራት በአምስት ዙር በዓለም የምግብ ፕሮግራም መስፈርት መሰረት ድጋፍ መደረጉን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽር ዘላለም ልጃለም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡
በዚህ ወር ብቻ ለ661 ሺህ 700 ተፈናቃዮች 101 ሺህ 800 ኩንታል እህል ለአምስተኛ ጊዜ ተደራሽ መሆኑን ነው ኮሚሽሩ የገለጹት፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ዝቋላ ወረዳ ለሚገኙ እናቶች እና ሕጻናት ለሁለት ወር የሚኾን 647 ኩንታል አልሚ ምግብ መላኩንም አንስተዋል፡፡
ይኹን እንጅ አዳዲስ ተፈናቃዮችን በማስተናገድ በኩል ችግር እያጋጠመ መኾኑን ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት፡፡ የምግብ ፍላጎት ለረጅ ድርጅቶች ከቀረበ በኋላ የሚመጡ ተፈናቃዮች በቀጣይ ዙር ጥያቄ ቀርቦ ድጋፍ እስኪደረግ ለችግር መጋለጣቸውን ነው ያነሱት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምግብ አቅርቦቱ ፈጥኖ ያለመድረስና ድጋፉ የተሟላ አለመኾን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይም በዋግኽምራ የሚገኙ ተፈናቃዮች አኹንም በአስቸጋሪ ውስጥ እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት የተለያዩ ተቋማት የተካተቱበት ግብረ ኀይል ‹(ኢንሲደንት ኮማንድ ፖስት) በማቋቋም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ ዞኖች መላኩን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ችግሮቹን በመለየት መፍትሔ ይሰጣል፤ ለአዳዲስ ተፈናቃዮችም ድጋፍ እንደሚሰጥ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መጠለያ፣ አልባሳት እና ማብሰያ እቃ የማቅረብ ኀላፊነቱን አለመወጣቱንና ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የፌደራል መንግሥት በጠላት ቁጥር ሥር የሚገኙ አካባቢዎችን ነፃ በማድረግ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የትብብር እንጂ የፉክክር ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ አይጠቅምም” ዶክተር ባምላክ ይደግ
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማስተዋወቅ የሚያስችል የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል አቋቋመ።