“የትብብር እንጂ የፉክክር ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ አይጠቅምም” ዶክተር ባምላክ ይደግ

176

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ የራሱ የኾነ የፖለቲካ ባሕል ሊኖረው እንደሚገባም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ባምላክ ይደግ ተናግረዋል፡፡
የሰከነ ፖለቲካ የጸናች ሀገር ይሠራል፡፡ የጸናች ሀገር የገዘፈ ታሪክ ይኖራታል፡፡ የሰከኑ መሪዎችና የበሰለ አስተሳሰባቸው ሀገርን ታላቅ ያደርጋል፡፡ ሀገር መሪዎቿን የምትመስልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ብልህና አርቆ አሳቢ ሲኖራት አሸናፊ የሆነ ውጤት ላይ ትደርሳለች፡፡ ያልሰከነ ፖለቲካ ደግሞ ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኀላፊ ዶክተር ባምላክ ይደግ ዓለምን እዚህ ያደረሷት መሪዎች ናቸው፣ መሪነት ጥንቃቄ የሚፈልግ፣ ኀላፊነት የሚሰማው፣ ተጠያቂነትን የሚቀበል፣ ሰብዓዊ መብትን የሚያከብር፣ የዜጎችን ጥያቄ የሚመልስ ኾደ ሰፊ የኾነ ነው ብለዋል፡፡ በኾነ ባልሆነው የሚቆጣ ወይም የሚፎክር መሪ ለአንድ ሀገር ሊጠቅም አይችልም ነው ያሉት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ሆደ ሰፊና ልዩነትን አምኖ የሚቀበል መሪ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ልዩነት ላይ በሰፊው ስለተሠራ ለሀገር አንድነትና ለሀገር ኅልውና የሚሠራ መሪ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ሀገራዊ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎች ሀገርን ይቀይራሉ፡፡ ከዛ ውጭ ግን ሀገርን አደጋ ውስጥ ይጥላልም ብለዋል፡፡
ግጭት ቀስቃሽ የኾኑ ጉዳዮችን በትዕግስት ማለፍና አርቆ ማሰብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ መሪዎች ሰዎች ለምን በግፍ ተገደሉ? የሚለው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል እንጂ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ እሽቅድምድም የትም እንደማያደርስም ተናግረዋል፡፡ ለወንጀለኞች ጠበቃ ከመቆም ይልቅ፣ ችግሩን አጣርቶ መፍትሔ መስጠት አዋጪው መንገድ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ሀገርን ለመገንባት ከሚወሰዱ መስዋእትነቶች እንደ መንግሥት ትዕግስት አንደኛው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ስሜታዊ የኾነ ምላሽ መስጠት ሀገር የማፍረስ ሂደትን ያፋጥን ካልሆነ በስተቀር ጥቅም እንደማይኖረውም አስታውቀዋል፡፡
መረጃ መሰብሰብ፣ መተንተንና በሕዝብ ላይ አደጋ በሚጥሉ ጉዮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አቋም መያዝ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ መሪዎች ኀላፊነት ሊሰማቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡ መሪዎች ተጠያቂነት እንደሚኖርም ማሰብ አለባቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ከክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመኾን መረጃ ማጣራት፣ መተንተን እና እርምጃ እንዲወሰድ መግፋት ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡ ትዕግስት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ እንደኾነ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ዝምታ ግን የመንግሥት ድክመት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የፉክክር ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን የትም እንደማያደርሳትም ተናግረዋል፡፡ የፉክክር ፌደራሊዝም አንተ ከእኔ በምን ትበልጣለህ፣ እኔ ካንተ እበልጣለሁ፣ አንተ ከእኔ ታንሳለህ የሚል፣ የሚያፎካክር እና ወደ አልተገባ ጉዳይ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ነው፡፡ ሀገራት የፉክክር ፌደራሊዝምን ሞክረውት እንዳልተሳካላቸውም አንስተዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም የተሳካላቸውና ለኢትዮጵያ አዋጩ የትብብር ፌደራሊዝም መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የትብብር ፌደራሊዝም አንደኛው ክልል ከሌላው ክልል ጋር በጋራ እንዲሠራ የሚያስገድድ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ አንደኛው ሌላኛውን እየወነጀለ የሚኖርበት የፉክክር ፌደራሊዝም ጤናማ አለመኾኑንም አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡ የፌደራሊዝም ሥርዓቱ ጤናማ እንዲኾን ከተፈለገ ክልሎች የሚተባበሩበት ማዕቀፍ መዘርጋት አለበት ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት አለበት ያሉት ዶክተር ባምላክ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ክፍተት ያየው የለም፣ በመካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ካልተቻለ አለመተማመን እየገዘፈ እንደሚሄድም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝብ ቀርቦ መሥራት መቻል አለበትም ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ለሕዝብ የቀረበ ካልኾነ ባይኖርስ የሚል ሃሳብ ከሕዝብ እንደሚነሳም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ወደ ሕዝብ በመቅረብ በኩል ኀላፊነቱን አለመወጣቱንም ገልጸዋል፡፡ መቀራረብ ከሌለ የከፋ ችግር እንደሚኖርም አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል መሪዎች ለቀጣይ ትውልድ የሚኾን ዕቅድ አላቸው ወይ? የሚለው ጉዳይም ሊጠየቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በአሥር፣ በሠላሳ፣ በሀምሳ እና በመቶ ዓመት ይሄን ግብ ነው የምናሳካው የሚል ዕቅድ ይዘው ወደ ሕዝባቸው ቢወርዱ የጋራ መግባባት ይመጣል፣ መገፋፋት አይኖርም፣ አቅም ያለውን ሰው መለየት ይቻላል ነው ያሉት፡፡
ውስጣዊና ውጫዊ የኾኑ ችግሮችን ለመፍታት መወያየትና አቅም ያላቸውን ሰዎች ማሠራት ሲቻል መኾኑንም አንስተዋል፡፡ አማራ ወጥ የኾነ የራሱ የፖለቲካ ባሕል ሊኖረው ይገባልም ብለዋል፡፡ ሕዝቡ አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ የተስማማ አስተሳሰብ ይዞ መደራጀት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ፖለቲከኞቹ ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ በእኩልነት መሥራት ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ ፖለቲከኞቹ እርሰ በእርስ በመግባባት ሕዝብን አንድ የሚያደርግ ነገር እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም።
Next articleየአርሶ አደሩ መራራ ሕይወት በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ።