የሜቴክ የቀድሞ የሥራ ኀላፊዎች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው።

193

መጋቢት 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ በነበሩ በሜቴክ የቀድሞ የሥራ ኀላፊዎች ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁሩንዲ እና ሌተናል ኮሎኔል አሰፋ ዮሐንስን ጨምሮ በሦስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው፡፡

ተከሳሾች ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል፣ የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት እና የሕዝብ እና የመንግሥትን ጥቅም የጎዳ ተግባር በመፈጸም የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1) (ሀ)፣ 33 እና 407 (1) (ሀ)፡ (2) ፡(3) ፤ 411 (1) (ሀ)(ሐ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፋቸው ነው ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉት።

ተከሳሾቹ የቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮርፖሬት ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ኀላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁሩንዲ߹ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል አሰፋ ዮሐንስ እና የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ እንዲሁም በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ቲምስ ኢንተርናሽናል (ሆ.ኮ) ኩባ. ሊሚትድ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና ያልተያዙት ዩዋን ሐን ናቸው።

ተከሳሾች በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ በኀላፊነት ደረጃዎች ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ኾነው ሲሠሩ ለጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ የሚያገለግል ግዥ ለመፈጸም ከጨረታ ውጪ እና በመመሪያው የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ግዥዉን ያለ ግልፅ ጨረታ መፈጸማቸው ተጠቅሷል።

በዚህም በውሉ የተመለከተው የሥራ አፈጻጸም የባንክ ዋስትና ባልቀረበበት ሁኔታ ክፍያ በመፈፀም እንዲሁም ከጠቅላላ የውሉ ዋጋ 10 በመቶ በዋስትና መልክ መያዝ የነበረበትን 5 ሚሊየን 564 ሺህ ዶላር ገንዘብ ባለመያዝ፣ ሥራው ሳይጠናቀቅ ጠቅላላ ክፍያው ሙሉ በሙሉ እንዲከፈል በማድረግ እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ ሥራውን ሳይጨርስ ፕሮጀክቱ ገና በ63 ነጥብ 14 በመቶ ደረጃ ላይ እያለ በራሱ ጊዜ አቋርጦ በመውጣቱ፥ ላልተሠራ ሥራ 422 ሚሊየን 791 ሺህ 908 ነጥብ 47 ብር አላግባብ በመክፈል መንግሥት ፕሮጀክቱን ለማጠናቅቅ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሰረት አላግባብ 6 ሚሊየን 400 ሺህ ዶላር ተጨማሪ ወጪ በመዳረጉ፤ ስልጣንን አላግባብ በመገልገል፣ የሙስና ወንጀል በመፈፀም በሚሉ በርካታ ክሶች በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡

ካልተያዘው 4ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት ሌሎች 3 ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ዝርዝር የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በማስረዳቱና ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃዎች ያላስተባበለ መሆኑን የተቸው ችሎቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመኾኑ የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኅብረተሰቡ ጥያቄዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ኹሉም መረባረብ እንደሚጠበቅበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡
Next articleበአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም።