
መጋቢት 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ሰሞኑን ያካሄዱትን ውይይት አስመልክተው በሰጡት ሐሳብ እንዳሉት ከኅብረተሰቡ የተነሱትን ጥያቄዎችን አዳምጠዋል፡፡ ለመፍትሔውም ኹሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰሞኑን በየምርጫ ክልላቸው ተገኝተው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በአንገብጋቢ እና ወሳኝ ወቅታዊ ጉዳዮች ከተወያዩ በኋላ ሪፖርታቸውን የጋራ ለማድረግ መክረዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ በየምርጫ ክልላቸው የሚገኘው ሕዝብ ሐሳቡን በነጻነት እንዳነሳላቸው ገልጸው ከየማኅበረሰቡ የተነሱትን ጥያቄዎች በየደረጃው ካሉ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመነጋገር ግብረ-መልስ ጭምር እየሰጡ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ሕዝቡ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረት እየጨመረ መምጣቱን፣ የተጀመሩ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች በጊዜ አለመጠናቀቃቸውን፣ በየአካባቢው የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን፤ የመብራት፣ የውኃና የቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ችግር መኖሩን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ስንዴን በመስኖ ለማምረት የማዳበሪያ፣ የነዳጅ እጥረት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መኖራቸውን እንደጠቆማቸው ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደከዚህ ቀደሙ በማወያየት ብቻ ይቀራል የሚል ጥርጣሬ ስላለ ሪፖርቱን በማጠናከር በየደረጃው ላሉ አስፈጻሚ አካላት በመላክ ክትትል እና ቁጥጥራቸው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በምክክሩ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዳሉት የምክር ቤቱ አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ በዋጋ ግሽበትና በኑሮ ውድነት፣ በመልካም አሥተዳደር ፣ በመሠረተ-ልማት እና በአጠቃላይ የልማት ጉዳዮች ላይ በየምርጫ ክልላቸው መክረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ከሕዝቡ የተነሱት ጥያቄዎች በመንግሥት ብቻ የሚመለሱ እንዳልኾነ ጠቁመው በኹሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ መፍትሔ ሊመጣ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ‘’የሕዝቡን ጥያቄዎች መንግሥት አይፈታቸውም’’ የሚለውን ጥርጣሬ ለማስወገድ የምክር ቤት አባላት የክትትል እና ቁጥጥር ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው አቶ ተስፋዬ ያስገነዘቡት፡፡
በኅብረተሰቡ የተነሱትን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች፤ የመብራት፣ የውኃ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ተደራሽነትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን፣ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑንም ዋና የመንግሥት ተጠሪው ገልጸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ የኑሮ ውድነት የተፈጠረው በዓለም-አቀፍ ክስተቶች ማለትም በአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ቢኾንም፣ እንደ ስንዴና ዘይት የመሳሰሉትን የምግብ ሸቀጦች እጥረት ለመፍታት መንግሥት ከውጭ ገዝቶ እያስገባ ስለኾነ ችግሩ እንደሚቃለል እምነታቸው እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በቀጣይነት ለመመለስም ምክር ቤቱ እቅድ አውጥቶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመው፣ ለምላሹ ግን ኹሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/