
መጋቢት 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እውነት ወደ ዘር ስታጋድል፣ በዘመነኞች ስትበደል፣ ውሸት ሲጎለምስ፣ እውነት ስትኮስስ ማየት ልምድ የኾነ ይመስላል፡፡ አፍና ሀብት ያላቸው ሀገራት እውነትን የጥቅማቸው እስረኛ ሊያደርጓት፣ አቅሟን ሊነጥቋት ይሻሉ፡፡ እውነት ከሙታን ተለይታ እንደምትወጣ፣ በጨለማ ውስጥ ላለው ብርሃን እንደምታወጣ፣ ነጻነት እንደምታመጣ አላወቁም፡፡ እውነት የያዘ ሞት አያሸንፈውም፣ መሰደድ አያጠፋውም፡፡ እውነት ጠንካራ ናት ብትቀጥንም አትበጠስም፣ እውነት ረቂቅ ናት ብትዘገይም አትረሳም፣ እውነት ኀያል ናት በውሸት መርግ ተሸፍና አትቀርም፡፡ እንደ ጭራ ቀጥናም ቢኾን አትበጠስም፡፡
የአዶልፍ ሂትለር ሥርዐት ጀርመናዊውያን ንጹሕ ዘር ናቸው ይል ነበር፡፡ ንጹሕ የኾነው ጀርመናዊ ደግሞ በንጽሕና ከኹሉም ከፍ ብሎ መቀመጥ አለበት አሉ፡፡ በዚያች ምድር ጉልበታም መንግሥት ስልጣን ይዞ ነበር፡፡ በዚያ ጉልበታም መንግሥት በሚመራት ሀገር እንዳይኖር የተፈረደበት ዘር ነበር፡፡ ዘሩ መጥፋት አለበት ተበሎ ተወስኗል፡፡ ያን ዘር ለማጥፋት ደግሞ ያለ ርህራሄ መጨፍጨፍ፣ ማሰቃየት አስፈላጊ ነው ብለው ተነሱ፡፡
እ.ኤ.አ 1938 በወርኃ ኅዳር የናዚ ወታደሮች አይሁዳውያን ወደ አሉበት አቀኑ፡፡ የሞት ሰይፍ አስለው፣ የጨከነ ልብ ይዘው፣ በጨከነ እጃቸው ሊገድሏቸው ገሰገሱ፡፡ መላ ጀርመን የሚገኙ አይሁዶች የሞት ሰይፍ ተስሎላቸዋል፡፡ ሰይፉ ሊበላቸው፣ ሰይፍ የያዙትም ሊቀሏቸው ቋምጠዋል፡፡ አይሁዶቹም እንደሚታረድ በሬ የመሞቻ ጊዜያቸውን እየጠበቁ ነው፡፡
ʺ ዛሬ እሞት ነገ እሞት አላውቀውም እኔ
ቢላ እየተሳለ ጭድ ይበላል በሬ”
እንደሚባለው ገዳዮች ዝግጅታቸውን ጨርሰው ተገዳዮች በየቤቶቻቸው መኖርን እያሰቡ ተቀምጠዋል፡፡ መቼ እንደሚሞቱ አያውቁም፡፡ ሞታቸውን የሚያዉቁት ገዳዮቻቸው ብቻ ናቸው፡፡
በዚያም ጊዜ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ ትዕዛዝ ተቀባዮችም ተፋጠኑ፡፡ የአይሁድ ሙክራቦች፣ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች በናዚዎች ትዕዛዝ ወደሙ፡፡ ማን ተው ይላል፡፡ ዝም ነው መልሱ፡፡ ሂትለር እስራኤላውያንን ከምድረ ገጽ ማስወገድ የሚል ዕቅድ አቅዷል፡፡
ማጎሪያ ቤቶች በጀርመን ተዘጋጁ፣ እስራኤላውያንም እየተለቀሙ ወደ ማጎሪያ ቤቶች ይጋዙ ጀመር፡፡ በማጎሪያ ቤቶች ታስሮ መውጣት፣ ታርሞ ማለፍ የለም፡፡ ታጉሮ መገደል እንጂ፡፡ ከኹሉም የከፋው ማጎሪያ ደግሞ ኦሽዊትዝ የሚባለው እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህ ማጎሪያ ሥፍራ የበደል በደል ይፈጸም ጀመር፡፡ በጋዝ ታፍነው ተገደሉ፣ በጣር ውስጥ ተሰቃዩ፡፡ ኦሽዊትዝን የምድር ገሃነብ ይሉታል፡፡ ነብስ ይበላበታል፣ የጣር ድምጽ ይሰማበታል፣ የሰው ስጋ ይጠበስበታል፣ ጭንቀት ነግሷል፣ ሞት እያስገመገመ ነው፣ ለሞት አፍ የተዘጋጁ ነብሶች ደግሞ ለመበላት ተቀምጠዋል፡፡
አይሁዳውያን የጀርመናውያን ችግሮች ናቸው ተብሎ የተሰበከው ስብከት ከፍ ብሎ ወደ አረመኔነት ተሻገገረና ሕዝብ በግፍ አለቀ፡፡ በሰው ልጅ ላይ መከራ ጸና፡፡ አይሁዳውያን ልብሳቸውን እያወለቁ ለሞት ወረፋ ያዙ፡፡ የጋዝ ክፍል ተዘጋጅቷል፡፡ ወደ ጋዝ ክፍሉም ገቡ፡፡ ክፍሉ የሚችለውን ካስገባ በኋላ የጋዝ ሞተሩ ይከፈታል፡፡ እነዚያ በጋዝ ውስጣ የገቡ ሰዎች በሲቃ ይጮሃሉ፣ የሚያስጨንቅ፣ የሚያስለቅስ ድምጽ ያወጣሉ፣ ነብሳቸውን ከሞት መንጋጋ የሚያወጣላቸው ኀይል ይገኝ ዘንድ ያለቅሳሉ፣ ይማጸናሉ፡፡ በዚያ ሥፍራ ግን ከሞት ውጭ የሚደርስ አልነበረም፡፡ ሞት ይዟቸው ይጠፋል፡፡ ሰዎች በጋዝ ታፍነው መሞታቸው እንደተረጋገጠ፣ ተረኞቹ ይገባሉ፡፡ እንዲህ እየኾነ አይሁዳውያን የአረመኔነትን ጥግ አዩት፡፡
የጀመርን ዶክተሮች በሰዎች ላይ ምርምር አደረጉ፣ በሰዎች ስብ ብርሃን ለማግኘት ሲሉ ሰዎችን እያሰቃዩ ሞከሩ፡፡ ናዚዎች የሰው ነብስ ቀጠፉ፡፡ ብዙዎች አልቀው ሌላ ዘመን መጣ፡፡ የሂትለር ዘመን አበቃ፡፡ የሂትለር ሐሳብና እቅድም የተወገዘ ኾነ፡፡ ዓለምም ናዚዎች ያደረሱት ግፍ ድጋሜ በዓለም እንዳይከሰት ስትል ኮነነች፡፡ የናዚን ሐሳብ የሚደግፍ ኹሉ ይወገዛል፣ መወገዝ ብቻ ሳይኾን በሕግ ይጠየቃል አለች፡፡
ዓለም ያለፉትን ገዳዮች የኮነነች ብትመስልም የአሁኖቹን ገዳዮችን ግን የምትኮንን አትመስልም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በጥላቻ የተነሳው አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን የሚወደውን፣ ለክብሯና ለፍቅሯ ሲል አያሌ መስዋእትነት የከፈለውን አንድ ሕዝብ ያጠፋ ዘንድ ወደደ፡፡ ለእርምጃዬ፣ ለሥራዬና ለእቅዴ መሰናክል የሚኾነኝ አንድ ሕዝብ አለብኝ አለ፡፡ ያም ሕዝብ የአማራ ሕዝብ ነው፡፡ የአማራን ሕዝብ የሚመስሉ ሌሎችም በምድር መኖር የለባቸው ሲል አሰበ፡፡
የሽብር ቡድኑ ዘመኑን ያረዝም ዘንድ መጥፋት አለበት ብሎ የሚያምነውን ሕዝብ በተለያየ ስልት ፈጸመ፡፡ ብዙዎችን አኮላሻቸው፣ ብዙዎችን ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አሥሮ ብርሃን አሳጥቶ እስከ ወዲያኛው ሸኛቸው፣ ከርስትና ከጉልታቸው እያፈናቀለ ስደተኛ አደረጋቸው፣ ሌሎችን ደግሞ እየሰበሰበ በጅምላ ረሸናቸው፣ በአንድ ላይ ቀበራቸው፡፡
የጎንደር ዪኒቨርሲቲ ከሰሞኑ አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን አግኝቻለሁ ብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የሽብር ቡድኑ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሐንን አፅም አስወጥቷል። “የኢትዮጵያዊው ኦሽዊትዝ” ብለው በሰየሙት በዚህ አሰቃቂ ሥፍራ ብዙዎች በግፍ አልቀዋል፡፡
ያ ምድር በማንነታቸው ብቻ በተገደሉ ንጹሐን አማራዎች ደም ርሷል፣ በዚያ ምድር የአማራዎች አጥንት በግፍ ተከስክሷል፡፡ በዚያ እስር ቤት በየቀኑ ሰዎች ይገደሉ ነበር፡፡ ገሚሶቹ በጅምላ ሲቀበሩ፣ የተቀሩት በቃሌማ ወንዝ ይጣሉ ነበር፡፡ ክብር ያለው ሰው እንደ ዘበት ተጣለ፡፡ አማራዎች በርስታቸው እንዳይኖሩ ተፈረደባቸው፡፡ የግፈኞች ሰይፍ በላቸው፡፡ የተከፈተው መቃብር ዋጣቸው፡፡ የራሳቸውን መቃብር እያስቆፈሩ እየገደሉ ይቀብሯቸው እንደነበርም ጥናቱ አመላክቷል፡፡
እነዚያ በደል ያልተገኘባቸው አማራዎች በድንጋይ በተዘጋ ጉድጓድ ውስጥ ይታሰሩ ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ኹልጊዜም ሞት አለ፡፡ በሚሞቱት ሰዎች የሚተካ ደግሞ አዲስ እስረኛ ይመጣል፡፡ ያም ይሞታል፡፡ ሌላ ይተካል፡፡ ያም እንደዚያው ይሖናል፡፡ ዘር ማጥፋት ነውና ዓላማው የሚታሰረውና የሚሞተው አያቋርጥም ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ውስጥ ሲታሰሩ የነበሩትን ቶሎ ቶሎ አስወግዷቸው የሚል ትዕዛዝ ይመጣ እንደነበርም ጥናቱ ያስረዳል፡፡ የጥናት ቡድኑ ሌሎች የጅምላ መቃብሮችን ለማግኘት አሰሳ እያደረገ መኾኑንና የዘር ፍጅት የተደረገበትን መረጃ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑንም አስታውቋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ገድየ እጨርሰዋለሁ ያለው ሕዝብ እውነት፣ ጀግንነትና ጽናት አለውና በሞቱ ገዳዮችን ገደላቸው፣ በሞቱ እቅዳቸውን አከሸፈባቸው፣ በሞቱ ዘመናቸውን ቋጨባቸው፡፡ ጠባሳው ግን በጥቁር መዝገብ ሰፍሮ ይኖራል፡፡ የደረሰው ጥፋት በስሕተት ሳይኾን በዕቅድ ስለ ነበር አይረሳም፡፡ ከዓመታት በፊት በጀርመን የተደረገው ግፍ ዛሬ ላይ በዓለም ይወገዛል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም እንዲዳኙ ተደርገዋል፡፡
እንደ ናዚ ኹሉ አሸባሪው ሕወሓት በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት ፈጽሟል፡፡ ዓለም ስለሞቱት ንጹሐን ያለችው ነገር የለም፤ አልኮነነችም፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎቹ ላይ ክስ በመመስረት ዓለምአቀፍ ፍትሕ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል፡፡
አንድ ነገር ግን እመን እውነት እንደምታሸነፍ፣ እውነት እንደ ማትበጠስ፣ እውነተኛ ስትኾን ብዙዎች ይገፉሃል፣ ያዳፉሃል፣ በግፍ ይገድሉሃል፣ ዳሩ የመጨረሻውን የድል ዋንጫ የምትወስደው አንተ ነህ፡፡ አንተ ብቻ ከእውነት መስመር አትዛነፍ፣ ከሰውነት ክብር አትለፍ፡፡ በዚያ ገሃነብ በተባለ ሥፍራ የሞቱት፣ ያለቀሱት፣ የሲቃ ድምጽ ያሰሙት፣ በግፍ ያለቁት እውነት በአጥፊዎች ላይ ይፈርዳል፡፡ የእውነት አምላክም ያግዛል፡፡ ዳግም ንጹሐን እንዳይሞቱ፣ የጅምላ መቃብር እንዳይኖር፣ ግፈኞች በንጹሐን ላይ እንዳይሰለጥኑ አንድነትን ምረጥ፣ ተስፋን ሰንቅ፣ ለእውነት ቁም፡፡ አንድ ስትኾን ዛሬ የካዱህ ነገ ይቀርቡሃል፣ አንድ ስትኾን ዛሬ የገፉህ ነገ እናግዝህ ይሉሃል፡፡ አንድነትህ መዳኛህ ነውና አንድ ኹን፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/