“የወልድያ-ቆቦ-አላማጣ መንገድ አልተዘጋም::” ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች

429

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2012 ዓ/ም (አብመድ) የወልድያ-ቆቦ-አላማጣ መንገድ እንደተዘጋ ተደርጎ የሚወራው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

ከሰሞኑ አንዳንድ የብዙኃን መገናኛ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አንስቶ በአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ-አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ ዓመታት እንደተቆጠሩ እየዘገቡ ነው፡፡ አብመድ ከተለያዩ ምንጮች ባደረገው ማጣራት ግን መንገዱ ዝግ አይደለም፤ የተለመዱ እንቅስቃሴዎችም እንደቀጠሉ መሆናቸውን ተረድቷል፡፡

በትግራይ ክልል የአላማጣ ከተማ ነዋሪው አቶ ጌታነህ ካሳ ለአብመድ እንደተናገሩት ከዓመት በፊት አላማጣ አካባቢ የፀጥታ ችግር አጋጥሞ እያለ ከተፈጠረ መስተጓጎል በስቀር እንቅስቃሴ የሚያስቆም ሁኔታ አልታዘቡም፡፡ ‹‹እኔ እንደማውቀው የተዘጋ መንገድ የለም፤ ወደ ወልድያም ሆነ ቆቦ መኪኖች ይመላለሳሉ፤ የአላማጣና የቆቦ፣ ወልድያ ሕዝብ እኮ አንድ ነው፤ በልቅሶውም በሰርጉም እንገናኛለን፤ እኔ መንገድ ተዘግቷል እሚለውን አሁን አንተ ስትጠይቀኝ መስማቴ ነው›› ብለዋል አቶ ጌታነህ፡፡

አቶ መርጊያው ተካ የተባሉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ‹‹ከመቀሌ-አላማጣ-ቆቦ -ደሴ -አዲስ አበባ የተዘጋ መንገድ የለም፡፡ ከዓመት በፊት አላማጣ በተነሳ ችግር ለቀናት ከነበረ ግርግር በስተቀር መንገዱም ግንኙነታችንም ሠላማዊ ነው፤ ማንኛውም ተሽከርካሪ እያለፈ ነው›› ብለዋል፡፡ የአላማጣና የራያ አካባቢ ኅብረተሰብ አንድነቱ የጠነከረና በደስታና በሐዘን የማይለያይ መሆኑን የተናገሩት አቶ መርጊያው ‹‹በፖለቲከኞች መካከል ችግር እንዳለ እንሰማለን፤ በኛ መካከል ግን ኮሽታም የለብን፤ አብረን ኑሯችን እየመራን ነው›› ብለዋል፡፡ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አለመቆሙንና ከየመናኸሪያዎቹ የተለመዱ ስምሪቶች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡ የሕዝብ ማመላለሻም ሆነ ሌሎች ተሽከርካሪዎች ያለምንም ገደብ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአላማጣ ከተማ የመንገድ ትራፊክ ኃላፊ ኢንስፔክተር ካኅሳይ ኅሉፍ ለአብመድ በሰጡት መረጃ ደግሞ ‹‹የአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ መንገድ ዝግ አይደለም፤ መለስተኛና አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች በአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ- ደሴ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከባድ መኪኖች ግን ከዓመት በፊት አጋጥሞ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ስጋት ስላላቸው ይመስለኛል በአላማጣ-ቆቦ አድርገው ወልድያ ሳይገቡ በአፋር በኩል ነው ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱት፡፡ መንገዱ ግን መዘጋቱን አልሰማሁም›› ብለዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከአካባቢው ተገኝቶ ባደረገው ማጣራትም መንገዱ አለመዘጋቱን አረጋግጧል፡፡ የከባድ ጭነትም ይሁን መለስተኛ እና አነስተኛ ሽከርካሪዎችም በአላማጣ-ቆቦ አድርገው ወልድያ እንደሚገቡ፣ አልፈው እንደሚሄዱ እና እንደሚመላለሱም ታዝበዋል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 9 መሠረት ክልሎችን ከክልሎች የሚያገናኙ መንገዶች ባለቤትነታቸው የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም መንገዱ እንደተባለው ስለመዘጋት አለመዘጋቱ መረጃ ካለው ለማረጋገጥ የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጠይቀን መረጃ እንደሌለውና ማጣራት እንደሚፈልግ አሳውቆናል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous articleኢትዮጵያ እና ጀርመን ለስድስት ዓመታት የሚቆይ የ21 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሙከራ ትግበራ ገቡ፡፡
Next articleየቡና ገለፈትን ከበካይነት ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይር የምርምር ውጤት ለቡና አብቃዮች ተዋወቀ።