
ደብረታቦር: መጋቢት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መሠረት የተጣለበት 11ኛ ዓመት በውይይት ተከብሯል።
ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እና ደቡብ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ባዘጋጁት ውይይት የግድቡ የግንባታ አፈጻጸም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የመላ ኢትዮጵያውያንን ርብርብ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ታደለ እሸቴ የግብጽ የውኃ ፖለቲካ በራስ ወዳድነት የተሞላና ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን አልሞ መሥራት ስለሆነ ሁሉንም ጫና ተቋቁመን ግድባችን እስኪጠናቀቅ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ.ር) እንደተናገሩት ከኃይል እጥረት ችግር ለመላቀቅ እና ከድህነት ለመውጣት ግድቡን መገንባት ፍትሐዊ እንደሚያደርገው ነው ያስረዱት። “የህዳሴ ግድብን ያህል ታላቅ ፕሮጀክት ያለ እርዳታ የምንገነባ መሆናችን፤ መታሰቡና መፈጸሙም የታላቅ ልዕልና ባለቤት መሆናችንን ይመሰክራል” ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሌሎችንም ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሥራት እንደምንችል ያረጋገጥንበትና አቅማችን የተገነባበት የአንድነታችን ማረጋገጫ እንደኾነም ነው ዶክተር አነጋግረኝ የገለጹት፡፡ ለህዳሴ ግድባችን ግንባታ ቀሪ ሥራዎች አቅማችን አጠናክረን እንድንቀጥል ሲሉም አሳስበዋል። ለህዳሴ ግድቡ ጉብኝትና ከሥራው ለመማር ለሚደረግ ፍላጎትም ዩኒቨርሲቲያቸው እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።
በህዳሴ ግድቡ ግንባታና ተግዳሮቶቹ ላይ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው የመወያያ ጽሑፍ ላይ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ግድቡ በፍጥነት ተገንብቶ ቢያልቅ በሀገራችን ላይ ያለው ጫና ሊቀንስ ይችላል፤ ለህዳሴው ግድብ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ መዋሉ ክትትል መደረግ አለበትም ብለዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ የውስጥና የውጭ ጫናን በመቋቋም ኹለተኛ ዙር ሙሌቱን አጠናቀንና ኃይል ማመንጨት መጀመራችን ኩራታችን ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ጠብቀን ለማቆየትም የአካባቢ ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ጥላሁን አስገንዝበዋል።
በውይይቱ የዞኑና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡-ዋሴ ባየ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/