ኢትዮጵያ እና ጀርመን ለስድስት ዓመታት የሚቆይ የ21 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሙከራ ትግበራ ገቡ፡፡

305

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2012 ዓ/ም (አብመድ) የኢትዮጵያ እና ጀርመን መንግሥታት የኢኮኖሚ ትብብር ባንክ በአማራ ክልል የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲለሙ ለማድረግ የሚያስችል የስድስት ዓመት ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሙከራ ትግበራ መግባታቸው ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ በደቡብ ወሎ ዞን የቦረና፣ ለጋንቦ፣ መሃል ሳይንት፣ መቅደላ፣ አማራ ሳይንት እና ተንታ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እሸቱ በተለይም ለአብመድ እንደተናገሩት አርሶ አደሮች ከወለድ ነጻ ብድር ተመቻችቶላቸው የተራቆቱ የወል መሬቶችን ተረክበው በደን እንዲሸፈኑ ይደረጋል፡፡

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮቹ አካባቢያቸውን በማልማትና የአካባቢውን ደንና ብዝኃ ሕይወት በመጠበቅ ከውጤቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው:: የሙከራ ትግበራውን ስኬታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአማራ ክልል የሚመለከታቸው ተቋማት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የየድርሻቸውን ወስደው እንዲሠሩ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ እንዲገባም የኢፌዴሪ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን እና ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው የስድስቱ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ባለፈው ዓመት መጋቢት በኮምቦልቻ ከተማ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው ነበር፡፡
ይህንን ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት የጀርመን መንግሥት የኢኮኖሚ ትብብር ባንክ 21 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል፡፡ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት 10 ሺህ ሄክታር መሬትን በደን በመሸፈን የብዝኃ ሕይወቱን ለመጠበቅ ከ50 ሺህ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሚለማው መሬት ውስጥ 2 ሺህ 500 ሄክታሩ ሀገር በቀል የችግኝ ዝርያዎች ይተከሉበታል፡፡

ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች የአደረጃጀትና የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደተጀመረም አቶ ጋሻው ገልፀዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በተጠቀሱት ወረዳዎች ውጤቱ ከታየ በኋላ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article21ኛዉ ዓመታዊ የጤና ዘርፍ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡
Next article“የወልድያ-ቆቦ-አላማጣ መንገድ አልተዘጋም::” ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች