
መጋቢት 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግናና ኩሩ የሚወለድብሽ፣ ፈሪ የማይፈጠርብሽ፣ ፍቅር የነገሰብሽ፣ ወተት እንደ ውኃ የሚቀዳብሽ፣ ምርት የሚታፈስብሽ፣ ስምሽ ከፍ ብሎ የሚጠራ፣ ጀግንነትሽ ለሀገር የሚያኮራ አንቺ የወርቋ ምድር እንደምን አለሽ? የተከዜ ዳሯ እመቤት፣ የበረሃዋ ንግሥት፣ የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ወልቃይት ኾይ እንደምን ከርመሻል? አንቺን ያልናፈቀ አልነበረም፡፡
ስምሽ ኃያል ነውና በተጠራሽ ቁጥር ወዳጅ ከመቀመጫው ተነስቶ ይፎክራል፣ ስምሽ ወደ ተጠራበት ንፍቅ ኹሉ ይጓዛል፡፡ ስምሽ ተጠርቶ ዝም ብሎ ማደር፣ ዝም ብሎ መዋል አልተቻለውምና የአንቺ ስም ሲጠራ ስምሽ ወደ አለበት፣ ክብርሽ ወደ ሚነገርበት ይሄዳል እንጂ፡፡
ብዙዎች በናፍቆት ተሰቃይተውልሻል፣ በምድርሽ ውስጥ ኾነው በባይተዋርነት ኖረውብሻል፡፡ በአንቺ ስም ብዙ ታይቷል፣ በአንቺ ኀይል ብዙ ተሠርቷል፡፡ ከአንቺ በፈለቀው ፍቅር እልፎች በፍቅር ተሳስረዋል፣ በአብሮነት ተጋምደዋል፣ ላይለያዩ ተማምለዋል፡፡ ከአንቺ በፈለቀው የቁጣ ማዕበል ክፉዎች ተጠርገው ተወስደዋል፣ ከነበሩበት ማማ ወርደዋል፡፡ የቆለሉት የውሸት ክብር ጥሏቸዋል፡፡ ክብርና ዝና ክዷቸዋል፡፡ አንቺ ኀያል ነሽ ወልቃይት፡፡
በስምሽ የሕዝብ አንድነት ጸንቷል፡፡ በስምሽ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ሲል በአንድነት ተነስቷል፡፡ በስምሽ ሞትን ንቋል፣ በስምሽ በባዶ እጁ እሳት ከጨበጠ ጋር ተጋጥሟል፡፡ ስምሽ ኀይል ኾኖት ድል ተቀዳጅቷል፡፡ በአንቺ ስም እሳት የጨበጠው ወድቋል፣ ተረትቷል፡፡
“ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” የሚለው ድምጽ ሲያገሳ ዙፋኑ ርዷል፣ ተንቀሳቅሷል፡፡ መጽናት አልችል ብሎ ወድቋል፡፡
ወልቃይት በአንቺ ስም የተዘጉት የጨለማ ቤቶች ተከፍተዋል፣ ለዓመታት ያለቀሱ እናቶች ስቀዋል፣ ጨለማ የበዛባቸው ብርሃን አይተዋል፣ እምየ ኢትዮጵያ እንዳይሉ የተከለከሉት ያለ ገደብ ጠርተዋል፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ እንዳሻቸው አውለብልበዋል፣ እጃቸው በሰንሰለት የተጠፈረው ተለቅቀዋል፣ ለአውሬ ሊሰጡ የነበሩት ድነዋል፣ ወጥተዋል፣ የተሰደዱት ወደሚወዷት ሀገራቸው ተመልሰዋል፣ ዱር ቤቴ ያሉት ወደ ቤታቸው ገብቷል፣
በአንቺ ስም ክፉዎች የእጃቸውን አግኝተዋል፣ ሲያሳድዱ የነበሩት በሥራቸው ተሳድደዋል፡፡ በአንቺ ስም የተገፉት ተደግፈዋል፣ የገፉት ተገፍተዋል፣ በአንቺ ስም አንገታቸውን የደፉት አቃንተዋል፣ በአንቺ ስም እልፍ ነገር ኾኗል፡፡
የስሜን በጌ ምድር ግዛት፣ የኢትዮጵያ መሠረት፣ የኹሉም እናት ወልቃይት ፍቅር የተራበውን በፍቅሯ ታጠግባለች፣ ጀግንነት ያማረውን ጀግንነቷን ታሳየለች፣ ማርና ወተት የተጠማውን በማር እያረሰረሰች፣ በወተት ታቀማጥላች፡፡ ፍቅር እንደ ወንዟ እንደ ተከዜ ያለማቋረጥ ይፈስስባታል፣ ሰሊጥና ማሽላ፣ ጥጥና አኩሪ አተር በማይገመገም አውድማ ይታፈስባታል፡፡ ለወዳጇ፣ ለሚወዳት ለሚያከብራት ፍቅር እንደሰጠች፣ ወተት እንዳጠጣች፣ በፍርንዱስ እንዳቀማጠለች፣ ጮማ እንደ ቆረጠች፣ ዓለም አሳይታ እንግዳ እንደተቀበለች ኹሉ ክብሯን ለሚነኳት፣ ማንነቷን ለሚዳፈሩባት ደግሞ ሌላም ስጦታ አላት፡፡
ድንበር የሚጥስ፣ ማንነት የሚያንኳስስ፣ ሃይማኖት የሚያረክስ፣ ርስት የሚወርስ ሲመጣ ደግሞ ተኩሰው በማይስቱ ልጆቿ ጥይት እንደ ቆሎ ታቆረጥማለች፣ ባሩድ እንደ ወተት ትግታለች፣ እርሳስ እንደ ጮማ ታጎርሳለች፡፡ ወልቃይት ውስጥ የፈለጉት ይገኛል፡፡ ፍቅር ለወደደ የማይነጥፍ ፍቅር፣ ጸብ ለወደደ ደግሞ የማይስት ጥይት፣ የማይታጠፍ ጀግንነት አለ፡፡
በወልቃይት ተኮሶ መሳት፣ ለፍቅር መሰሰት አይታወቅም፡፡ አፈሙዛቸው ዓይን አለው፡፡ አንጥሮ አይስትም፣ አሳልፎ አይሰድም፡፡ ሲመለስ እግሩን፣ ሲዞር ግንባሩን በለው እያሉ ይጥሉታል፡፡ ለዚያም ነው፡፡
“ስሜን በጌምድር ወልቃይት ጠገዴ፤
ከእኛ በላይ ላሳር የአተኳኮስ ዘዴ” የሚባለው፡፡ አተኳኮስ ከእነርሱ በላይ ላሳር ነው፡፡ ቢሻቸው ግንባሩን፣ እንዲያ ቢል አንገቱን፣ ዝቅ አድርገው እግሩን ከፈለጉበት ሥፍራ ላይ ለይተው ይመታሉ፡፡
በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣ ጠላት ኹሉ የእነዚያን የስሜን በጌምድር የወልቃይት ጠገዴን ጀግኖች ክንድ እየቀመሰ ተመልሷል፡፡ ስንዝር በማያላውሰው በዚያ ሞቃታማ ስፍራ ስንዝር የማያለውሱ ጀግኖች ይወለዳሉና ኹልጊዜም ጠላት እየተመታ ይመለሳል፡፡
ጀግኖቹ ከበረሃው የላቀ ይጋረፋሉ፣ ይጥላሉ እና አፈሙዛቸውን አልፎ የሚያልፍ የለም፡፡ በአንድ እጃቸው ጠመንጃ በአንድ እጃቸው ደግሞ እርፍ እየጨበጡ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከውጭ ጠላት ጠብቀዋታል፡፡ ሰላም ሲኾን ወደ ማረሻው፣ ክፉ ቀን ሲመጣ ወደ ጠመንጃው እያነዘነበሉ ሀገር አጽንተዋል፣ ታሪክ አስቀምጠዋል፡፡
ለሀገር መሠረት የኾነው ሕዝብና ሥፍራ ታዲያ በውጭ ጠላት ሳይደፈር፣ ለጠላቱም ሳይበገር ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ዳሩ ወገኔ የሚላቸው፣ ተከዜን ተሻግረው ወደቀየው ሲዘልቁ አንጥፎ የሚያስቀምጣቸው፣ ወተት በካቦ፣ ጠላ በገንቦ፣ ጮማ አስቆርጦ ብሉ የሚላቸው፣ መኝታቸውን ለቅቆ የሚያስተኛቸው፣ አቀማጥሎ የሚያስተናግዳቸው፣ አስተናግዶም ስንቅ አስይዞ ወደ መጡበት የሚሸኛቸው ከውጭ የሚመጣው ጠላት ሀገሩንና ሀገራቸውን ኢትዮጵያን እንዳይነካባቸው የሚጠብቅላቸው ሰዎች ከተከዜ ተሻግረው መጥተው በደል አደረሱበት፡፡
ሲያምናቸው ከዱት፣ ሲደግፋቸው ገፉት፣ ሲያጎርሳቸው ነከሱት፣ በእንግድነት መጥተው ባለ ርስት ነን አሉት፣ ባለ ርሰቱ፣ ባለ ጉልቱ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ተንገላታ፣ ቤቱን እንግዶች እንኑርበት፣ ጓሮውን እንግዶች እናምርትበት፣ የላሞቹን ወተት እኛ እንለባቸው፣ የበሬውን እሸት እኛ እንውሰደው አሉት፡፡ ያን ጊዜ ወልቃይ ተቆጣ፡፡ ያን ጊዜ ወልቃይት ከፋኝ አለ፡፡ ከፋኝ ብሎም አልቀረም፣ በርስቱና በማንነቱ የመጣበትን እንገዳ ኾኖ የገባን ጠላት አምርሮ ታገለው፡፡ በየጥሻው ጣለው፡፡
ትግሉ በአጭር ጊዜ የሚቋጭ አልነበረም፡፡ ዓመታት ሄዱ፡፡ የወልቃይት ቁጣ በመላው አማራ ተሰራጨ፣ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ሲል ከጫፍ ጫፍ አስተጋባ ያን ጊዜ ጠላት ተደናበረ፡፡ የሚይዘው ጠፋበት፡፡ በሚመቻው መንገድ አስምረው ያዘጋጁት ታጣቂ አቅም አነሰው፣ ማዕበሉን መቋቋም ተሳነው፡፡
የወልቃይት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አዲስ ነገር ይዞ መጣ፡፡ ለወትሮው ድልና ክብር የሚመጣባት ወልቃይት አኹንም የኢትዮጵያ የድል መነሻዋ እኔ ነኝ አለች፡፡ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ያሉት ወጣቶች ደረታቸውን ለጥይት እየሰጡ ከታጠቀ መንግሥት ጋር ተጋጠሙ፡፡ ወጣቶቹ እውነት፣ መንግሥት ደግሞ እሳት ይዞ ተጋጠሙ፡፡ እውነት እሳቱን አቀዝቅዞ ወጣቶቹ ባለ ድል ኾኑ፡፡
በወልቃይት ምድር ላይ እንግዳ ኾኖ መጥቶ ባለ ርስት ነኝ ሲል የነበረው ተከዜን ተሻግሮ ወደ ስፍራው አመራ፡፡ ወልቃይቶች እንግዳ መቀበልን ባሕላቸው ነው፣ እንኳን ከሚወዷት ሀገራቸው የመጣ ይቅርና ከውጭ የመጣንም እንግዳ ማስተናገድ ያውቃሉ፡፡ እንግዳ ኾኖ መጥቶ ባለቤቱ እኔ ነኝ የሚልን ግን አይታገሱም፡፡ ወልቃይቶች በእውነታቸው፣ በጀግንታቸውና በጽናታቸው በአባቶቻቸው ባድማ፣ በጸናች ማንነታቸው ተዋቡ፡፡ አማራዎች ናቸውና አማራ ነን አሉ፡፡ ይኽንንም በተግባር አሳዩ፡፡
ዛሬ ላይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አማራዎች በርስታቸው እና በማንነታቸው በሚፈልጉት መንገድ እየኖሩ ነው፡፡ ወልቃትን ሲናፍቋት፣ በአሻገር ኾነው ሲጠሯት፣ በስሟ ሲምሉ ሲገዘቱባት የነበሩት ወደ ምድሯ እየሄዱ ፍቅራቸውን እየተወጡ፣ አንድነታቸውንም እያጸኑ ነው፡፡ ተከዜ ላይ ዋኝተው፣ በዚያው በተከዜ ወንዝ ዳር አንድነታቸውን አጽነተው፣ ቃል ኪዳናቸውን አጥበቀው ይመለሳሉ፡፡
ወልቃይት የአማራ መሠረት፣ የአማራ አንድነት፣ የአማራ ጀግንት፣ የአማራ ብልሐትና ማንነት የሚገለጽባት ምድር ናት፡፡ የአማራ ወጣቶች ቀኜ ትርሳኝ ብለው ወደ ታገሉላት ምድር እየገሰገሱ ነው፡፡ በዚያ ውስጥ አንድነት፣ ጀግንት፣ ጽናት፣ አርቆ አሳቢነትና አሸናፊነት አለና፡፡
ወልቃይት ላይ እንገናኝ፡፡ ከተከዜ ዳር ቆመን፣ ዙሪያ ገባውን ተመልክተን፣ ሑመራ ላይ መክረን አንድነታችን እናጽና፡፡ አንድነትህን ለማጽናት፣ ብልሐትና ጀግንነትኽን ለማሳየት የሻትክ ና እጠብቅሃለሁ ወልቃይት ላይ እንገናኝ፡፡ ወልቃይት ላይ ተገናኝተን፣ የወርቋን ምድር ተመልክተን ቃል ኪዳናችንን አጽንተን፣ በቃላችን እንኖራለን፡፡ ወልቃይት ብዙ የታየበሽ፣ የሀገር ዘብ የኾንሽ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/