
ለመላው ኢትዮጵያውያን!
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዕለት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ እንኳን አብሮ አደረሰን።
እነሆ! . . . ለሺህ ዓመታት ሲፈስ የነበረው የዓባይ ወንዝ ለሀገራችን ሁነኛ የልማት አቅም ለመሆን በሩ የተከፈተበትን ታሪካዊ ዕለት በጋራ ለመዘከር አበቃን!
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ግድቡ ወሳኝ የግንባታ ሂደቶችን በማለፍ በአሁን ጊዜ የቅድመ ኀይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በዚህ ታሪካዊ የግንባታ ጉዞ የሕዝባችን ሁለገብ ድጋፍ፤ የመንግሥት ጠንካራ አመራር፤ የዲያስፖራ ወገኖቻችን እገዛ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ርብርብ በእጅጉ የሚደነቅ እና የሚያኮራ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ለደማቅ አበርክቷችሁ በመንግሥታችን እና በመላው የሀገራችን ሕዝብ ስም ከፍ ያለ ምስጋና እና አክብሮቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።
በቀጣይ ቀሪ የግንባታ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም የሰፊውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ እና ድጋፍ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
በሌላ በኩል በአሁን ወቅት በተለያየ መልክ የሚገለፁ ችግሮች ሀገራችንን እየፈተኗት ቢሆንም፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የተስተዋለውን የፀና ሕዝባዊ አንድነት እና ሕብረት የበለጠ አጠናክሮ በድል ማሻገር ይጠይቃል።
በመጨረሻም ከቀደሙ አባቶቻችን በወረስነውን የድል አድራጊነት ጠንካራ መንፈስ ለመጪው ትውልድ የታፈረች፣ የተከበረች እና የበለፀገች ሀገር ለማስረከብ አንድነታችንን እና ሕብረታችንን አጥብቀን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
“ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን ነው!”