እውነት አሸባሪው ትህነግ ከግጭት መራቅ ይሆንለታል?

193

ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ግጭት ለአሸባሪው ትህነግ ከዘመን የተመዘዘ ሥሪቱ ስለመሆኑ ደጋግመን ዐይተናል፡፡ ኢትዮጵያ በአሸባሪው ትህነግ ተወግታ፣ ደምታ የቆሰለችው አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ የሽብር ቡድኑ እንደ ድርጅት ከተመሰረተበት፣ እንደ ፓርቲ ከተቋቋመበት እና እንደ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ የግጭት በረዶ ያላዘነበበት ዘመን በስህተት እንኳን አይገኝም፡፡ አሸባሪው ትህነግ ለዘመናት በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ግጭት ጠማቂ ብቻ ሳይሆን አጋፋሪም ጭምር ነበር፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ችግር ምንጩ “ከእኔ ውጭ ወደ ውጪ” የሚለው ግትር አቋሙ ነው፡፡ መቻቻል፣ መነጋገር፣ አንጻራዊነት እና እውነት ለአሸባሪው ትህነግ የሚመቹ እሳቤዎች አይደሉም፡፡ ስለሰላም ሲባል ሌሎች አማራጮችን ማየት፣ ስለሕዝብ ደኅንነት ሲባል አፈሙዝ መዘቅዘቅን እና ስለሀገር ሲባል ሰጥቶ መቀበልን በሽምግልና ዘመኑ እንኳን አልተማረም፡፡ የሽብር ቡድኑ የሰላም አማራጮችን ተስቶት ከተቀበለ እንኳን የምንረዳው ሃቅ ቢኖር አማራጭ አልባ መውጫ ቀዳዳ ማጣቱን ነው፡፡
በተደጋጋሚ ግጭት በማያጣው የኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ፖለቲካ ውስጥ አሸባሪው ትህነግ የሰላም አማራጮችን የሚያቀርበው በአዞ እምባ ነው፡፡ በአሸባሪው ትህነግ ቤት ሰላም እንደአማራጭ ሆኖ የሚቀርበው ጊዜ መግዛት ሲፈልግ ብቻ ነው፡፡ የኃይል ብልጫ ያገኘ በመሰለው ጊዜም አምብቶ የተቀበለውን የሰላም አማራጭ እየቀለደ ለመናድ ማሰብን አይሻም፡፡ በአጭሩ አሸባሪው ትህነግ አቅም ካላጠረው በቀር ሰላም አማራጭ አልባ ምርጫ ነው ብሎ ያመነበትን ጊዜ የለም፡፡
ወቅታዊው የሀገሪቱ የሰላም ችግር ከመፈጠሩ ቀድሞ አሸባሪው ትህነግ ከፖለቲካዊ አማራጮች እስከ ሽምግልና ለሰላም እንዲሠራ ያልተለመነበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የሽብር ቡድኑ በሀገር ላይ ክህደት ፈጽሞ የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ከመግባቱ በፊት የፖለቲካ ልዩነትን በሃሳብ መፍታት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሮት ነበር፡፡ አሸባሪው ትህነግ “መብረቃዊ” ካለው የጦርነት ጅማሮው በኋላም ካለፉ ስህተቶች በመማር ቀሪ ችግሮችን በሰላም እንዲፈታ ተደጋጋሚ ሙከራ፣ በአንድ ወገን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ እና የሰላም ጥሪዎች ቀርበዋል፡፡ አሸባሪው ትህነግ ግን የቀረቡትን የሰላም አማራጮች ገልብጦ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስምባቸው እና ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ሲፈጥርባቸው ተስተውሏል፡፡
ከሰሞኑ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎቹ ሰብዓዊነት ሲል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ገልጿል፡፡ ጥያቄው ግን የሽብር ቡድኑ አባላትስ በተመሳሳይ ግጭት ለማቆም ይወስናሉ? የሚለው ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ማቆሙን ተከትሎ የሽብር ቡድኑ ዳግም ወረራ ቢፈጽም የፌድራል መንግሥቱ እና ክልሎች ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ትምሕርት ክፍል መምሕር እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ከሆኑት ሙሉነሽ ደሴ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሲባል ተደጋጋሚ “የተናጠል” አማራጮች ታይተዋል ሲሉ መምሕር ሙሉነሽ አንስተዋል፤ ሰላም የአንድ ወገን በጎ ፈቃድ አለመሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በአማራ እና አፋር ክልሎች ከደረሰው ወረራ መማር ግድ ይላል ነው ያሉት ምሁሯ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሯ እንዳብራሩት በቅርቡ የፌዴራል መንግሥቱ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ማቆሙ ጤነኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ከሽብር ቡድኑ ተፈጥሯዊ ሥሪት አንጻር ለትግራይ ሕዝብ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ይጠቀምበታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፤ እናም የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ክልሎች በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፤ በተለይም የአማራ እና አፋር ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግልጽ ውይይት እና ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሯ እንዳሉት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ከሚደርሰው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ የሽብር ቡድኑ በወረራ ከያዛቸው የአማራ ክልል እና አፋር ክልሎች ለቆ እንዲወጣ ቅድመ ግዴታ መግባት ይኖርበታል፤ ከዚያ ውጭ ግን አሁንም ድረስ በርካታ ወገኖችን በወረራ ውስጥ ጥሎ ለአንድ ወገን ሰብዓዊ ጉዳዮችን ማሰብ እንደ ትናንቱ ዋጋ ያስከፍላል፤ ካለፈው ወረራ በተለይም አማራ ክልል ብዙ መማር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች እንዳሉ ግልጽ ነው ሲሉ እጩ ዶክተር ሙሉነሽ አንስተዋል፡፡ ለሽብር ቡድኑ አቅም ከሚሆኑ “የተናጠል” ውሳኔዎች ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን ማተኮር ይበልጥ ተመራጭ ነው ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የሰላም ችግር ያለው የተሳሳተ አመለካከት ከኹለት አቅጣጫዎች የመነጩ ናቸው ይላሉ፡፡
የመጀመሪያው አሸባሪው ትህነግ በሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ከግለሰብ እስከ ቡድን፣ ከአህጉር እስከ ዓለም አቀፍ እና ከመንግሥታት እስከ ድርጅቶች የራሱን ሰዎች አስቀምጧል፡፡ እነዚህ የሽብር ቡድኑ ደላሎች በኢትዮጵያ ያለውን እውነት እያወቁ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተዛባ መልኩ እንደአስረዱም ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው መልኩ ያልተረዱ አሉ ነው የሚሉት መምሕርት ሙሉነሽ፡፡ ይህ የተፈጠረው ደግሞ ዲፕሎማሲያችን ይኽንን የማስረዳት እና የኢትዮጵያን እውነት በስፋት የማሳየት አቅም ጠንካራ አለመሆን ነው ይላሉ፡፡
ዶክተር ሙሉነሽ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ቁሳቁስ እንዲደርስ ካለ በጎ እሳቤ ጎን ለጎን የደኅንነት እና የሰላም ተግባርን በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ መምሕርት ሙሉነሽ ካለፉት ስህተቶች መማር የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልሎቹ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ነዋሪዎችን ለእንግልት የሚዳርጉና የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ አሠራሮችን ለማስወገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራ ነው” የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር
Next articleመንግሥት የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል አማራጭ እንዲፈጸሙ ሊያደርግ ነው፡፡