በአትሌቶች ተመራጭ የሆነ የአትሌቲክስ መንደር በጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ እየተገነባ ነው፡፡

258

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2012 ዓ/ም (አብመድ) በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙት የአትሌቲክስ ማስለጠኛ ቦታዎች ተመራጭ የተባለው የአትሌቲክስ መንደር በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ እየተገነባ መሆኑን የስፖርት ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2002 ዓ.ም በቀድሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ያሌው ጎበዜ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአትሌቲክስ መንድር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ አትሌቲክስ መንደሩ 84 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ ግንባታው 29 ሚሊዮን ብር እንደሚጨርስም ዕቅድ ተይዞለታል፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ አግልግሎት መስጠት ሲጀምር 360 አትሌቶች በመያዝ ስልጠና መስጠት እንደሚያስችል ታውቋል፡፡ በአትሌቲክስ መንደሩ በዚህ ወቅት 104 አትሌቶች ስልጠና ይወስዳሉ፡፡

ወጣት አዕምሮ ያለው በአትሌቲክስ መንደሩ ከሚሰለጥኑ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በየቀኑ ወደ ማዕከሉ በመመላለስ ስልጠና እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡ ‹‹የሀገሬን ሰንደቅ ዓላማ አንድ ቀን ከፍ አድርጎ የማውለብለብ ውስጣዊ ፍላጎት ስላለኝ በየቀኑ ከሩቅ ቦታ በመመላለስ የአትሌቲክስ ስልጠና እወስዳለሁ›› ብሏል ወጣቱ፡፡ በአትሌቲክስ መንደሩ ከሜዳው በዘለለ የአትሌቶች ማረፊ ተሰርቶ በአንድ መንደር ውስጥ ተሰባስበው ስልጠና ለመውሰድ እንዲያግዝ የግንባታው ሥራው ቶሎ ማለቅ እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

አቶ መብራቱ ይመር ደግሞ የቲሊሊ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የቲሊሊ አትሌቲክስ መንደር ተጠናቅቆ አግልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ ግንባተው ቶሎ ተጠናቅቆ አግልግሎት እንዲሰጥ ከኅብረተሰቡ እስከ 700 ሺህ ብር ለማሰባሰብ ቃል ተገብቶ ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙም ተናግርዋል፡፡ አዊልማ፣ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን እና የፌዴራል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እግዛ እያደረጉ እንደሚገኝም የተናገሩት የአካባቢ ነዋሪው ይህ ብቻም በቂ ባለመሆኑ ደግሞ በቅርቡ ቴሌቶን በማዘጋጀት አስፈላጊውን ገንዘብ በመሰብስብ ለአትሌቲክስ መንደሩ መፋጠን እገዛ ለማድርግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ መልስው ኑሬ የአዊልማ የአትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ታዋቂ አትሌቶች የፈለቁበት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አትሌት ጌታነህ ሞላ እና የኔው አላምረውን የመሳሰሉ አትሌቶች የወጡበት አካባቢ በመሆኑ የአካባቢ ወጣቶች በአትሌቲክስ ዘረፍ በስፋት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ወጣቶችም በአትሌቲክስ ዘርፍ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት በሳምንት ዘጠኝ ጊዜ ስልጠና እንደሚከታተሉ ነው አሰልጣኙ የተናገሩት፡፡ ሰልጣኞች ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ተሰባስበው የሚያርፉበት የአትሌቲክስ መንደር ተጠናቅቆ አግልግሎት አለመጀመሩ ስልጠናውን በአግባቡ ለማስኬድ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የስፖርት ጽሕፈት ቤት የስልጠናና ውድድር ባለሙያ አቶ ጌታነህ ታፈረ ‹‹በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ቦታዎች ተመራጭ የተባለው የአትሌቲክስ መንደር እየተገነባ ነው፡፡ አካባቢውን ተመራጭ ከሚያደርጉት መካከልም የቦታ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት ምቹ መሆን፣ ሜዳው በተፈጥሮ ወጣ ገባ መሆን፣ ውኃ አዘል፣ ዳገት፣ ጫካ፣ ተራራ እና ሌሎችም ምቹ የአትሌቲክስ ስልጠናን ውጤታማ የሚያደርጉ ግባቶች መኖራቸው ነው›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ደግሞ ከዚህ በፊት በአትሌቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በማዬት ልጆቹ በአትሌቲክስ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ አትሌቲክስ መንደሩን ከዚህ በፊት ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ በመጎብኘት ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደገቡ አስታውሰው ‹‹ቃል የተገባውን ገንዘብ በማሰባሰብ ግንባታው ለማፋጠን እንስራለን›› ብለዋል፡፡

የአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ በዚህ ወቅት 30 ከመቶ እንደደረሰና ቀሪ ግንባታው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንቲገኝ ጌጡ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleየግለሰቦች ግጭት ህልፈተ ህይዎትና የንብረት ጉዳት አስከተለ።
Next article21ኛዉ ዓመታዊ የጤና ዘርፍ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡