
መጋቢት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት አውራ ጎዳና ንዑስ ቀበሌ ላይ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻዲቅ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ ታደሰ ገብረጻዲቅ እንዳሉት ችግሩ የተፈጠረው በዞኑ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት አውራ ጎዳና ንዑስ ቀበሌ ላይ ነው፡፡ ታጣቂዎች ወደ ጅቡቲ የሚሄደውን መስመር ተከትለው ወደ አዳማ መስመር ሲያልፉ በሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት አውራ ጎዳና ንዑስ ቀበሌ ከተማው ላይ ሲደርሱ መሳሪያ በመተኮሳቸው ማኅበረሰቡ ያለበትን የጸጥታ ስጋት መሠረት አድርጎ ድርጊቱን ተቃውሟል፤ ለጸጥታ አካሉም ማሳወቁን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ ታጣቂዎቹ አልፈው ወደ አዳማ ከሄዱ በኋላ ሲመለሱ በድጋሚ መሳሪያ ሲተኩሱ በአካባቢው የነበረው የፌዴራል ፖሊስ ታጣቂዎቹን ለማነጋገር ሲሞክር ተኩሰ ከፍተው ጉዳት ካደረሱ በኋላ ወደ አካባቢው በመግባታቸው አለመረጋጋት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለይቶ ችግር ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡
በተፈጠረው ችግርም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት አቶ ታደሰ በተፈጠረው ችግርም ዞኑ ማዘኑን ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም በአካባቢው የተሰማራው ግብረኀይል አጣርቶ ጉዳቱን እንደሚያሳውቅ ነው ያስገነዘቡት፡፡
አቶ ታደሰ በአካባቢው የተለያዩ ግጭቶች የሚከሰቱ በመኾኑ እና የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ችግር የሚፈጥሩበት ቀጣና በመኾኑ ከኅብረተሰቡ እውቅና ውጭ የሚካሄድ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለግጭት ስለሚዳርግ በጥንቃቄ ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን እና የምሥራቅ ሸዋ ዞን ለሌሎችም ምሳሌ የሚኾን ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ዋና አሥተዳደሪው ችግሩ ከተፈጠረም በኋላ ዞኖቹ እየተነጋገሩ ችግሩን ለመሻገር እየሠሩ ስለመኾናቸው አብራርተዋል፡፡ ኹለቱ አጎራባች ሕዝቦች ወደፊትም አብረው የሚኖሩ በመኾናቸው እየተነጋገሩ ችግሩን የፈጠረውን አካል አጥንቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሰቡት፡፡
የተፈጠረውን ችግር ለማባባስ የሚጥሩ ኀይሎች ስለሚኖሩ በሰሜን ሸዋም በምሥራቅ ሸዋም ያሉ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ማኅበረሰቡ ተናበው እንዲሠሩ ዋና አሥተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/