
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ ራሱን ብዙ ጊዜ ሲደግም እየታዘብን ነው፡፡ ዛሬም የሰላም እጦታችንን እንደ ምክንያት፤ ድህነታችንን እንደጉልበት እየተጠቀሙ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ክንዶቻቸውን ሲያሳርፉብን እናስተውላለን፡፡ ሰብዓዊነት እንደ መነሻ፣ ዴሞክራሲ እንደ ሰበብ እና ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደ ምክንያት ቢቀርቡም ጉዳዩ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አዛዥ እና ናዛዥ መሆን የምትሻው አሜሪካ የወቅታዊው የኢትዮጵያ መንግሥት አካሄድ ደንቀራ የሆነባት ትመስላለች፡፡ በቀጣናው ለአፍታ እንኳን መራቅ የማይፈልጉት እና በዙሪያው የሚያንዣብቡት አንዳንድ ሀገራት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ዐይንና ናጫ ሆነዋል፡፡ በግልጽ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ መሻታቸው የሚዘውሩት ታዛዥ አሻንጉሊት አሥተዳደር መሰየም ፍላጎታቸው እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን መራሹ መንግሥት በልመና እና በብድር ስም ከሚመጣው ገንዘብ ገሚሱ የግል ኪሳቸውን የሚያሳብጠው ምዕራባዊያን የፖለቲካ ደላሎች ያ የፋሲካ ዘመን ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ይሻሉ፡፡
ከካይሮ እስከ ካርቱም፣ ከኒው ዮርክ እስከ ብራስልስ የተንሰላሰሉት ደላሎች ጉዳይ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በሚመለከት በተለያዩ ተቃውሞዎች ተመሳሳይ ፊቶችን የማየታችን እና የማይሻሻሉ ምክንያቶችን የመስማታችን ሚስጥሩ የግል ፍላጎት የሚንጠው ውስብስብ ሴራ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተቻለ እንዲቆም ካልተቻለ ደግሞ እንዲስተጓጎል የፀጥታው ምክር ቤት ከደርዘን በላይ እንዲሰባሰብ ሲወተውቱ የነበሩት የትሮይ ፈረሶቹ ኢትዮጵያ ከአግዋ እንድትታገድ ሲያስተባብሩም አስተውለናል፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የፌዴራል መንግሥት ከመቀሌ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ የሽብር ቡድኑ እስከ መሃል ሀገር ወረራ ሲፈጽም እነዚሁ የትሮይ ፈረሶች ከናይሮቢ እስከ አዲስ አበባ እየተሸከረከሩ መንገድ ጠራጊዎች ሲሆኑ ተመልክተናል፡፡
ሀገራቱ የሽብር ቡድኑ ወረራ በበርካታ የአማራ እና አፋር ክልሎች ዜጎች በጭካኔ ሲጨፈጨፉ፣ በጅምላ መቃብር ሲቀበሩ፣ እናቶችና ሕጻናት ሲደፈሩ፣ ትምሕርት ቤቶች ሲወድሙ፣ የጤና ተቋማት ሲዘረፉ እና የኢንዱስትሪ መንደሮች ሲጋዩ ዐይኖቻቸው አይተዋል፤ ጆሮዎቻቸው ሰምተዋል፤ ድርጊቱን አውግዘው ከፍትሕ፣ ከሰብዓዊነት፣ ከሰላም እና ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጎን መቆም አልቻሉም፤ ከዛ ይልቅ በኢምባሲዎቻቸው በኩል የሚዘውሯቸው እና የሚያሰራጯቸው የሽብር መረጃዎች ሌላ የትግል አውድማ ሲሆኑ ታዝበናል፡፡
35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ እንዳይካሄድ፣ የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ፣ የገቡትም በአስቸኳይ እንዲወጡ እና የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ከሀገር እንዲኮበልሉ ላይ ታች ባዝነዋል፤ የአማራ እና የአፋር ሕዝብ ተጨፈጨፈ ለሚለው ቅሬታ ጆሮ ዳባ ልበስ ነበር ምላሻቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንድናደርስ የድንበር አካባቢ በሮች ይከፈቱልን እያሉ ሲጠይቁ የነበሩት በጎ አድራጊዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነን ባዮቹ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለሰብዓዊ ድጋፍ እጆቻቸውን ለዘረጉ ንጹሃን የሚሆን እንጥፍጣፊ ምላሽ ግን አልነበራቸውም፡፡ የአማራ እና የአፋር ሕዝብ ሰቆቃ ለእነርሱ የሰብዓዊነት ጉዳያቸው አልነበረምና፡፡
የውጭ ኃይሎቹ ከ100 በላይ የሰብዓዊ ቁሳቁስ ጭነው መቀሌ የደረሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች መመለሳቸው የውኃ ሽታ ሲሆን እና የወራሪው ቡድን ወራሪ አባላቱ አመላላሽ ሲሆኑ ለምን ማለት አልፈለጉም፤ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢው ዘልቀው እንዲገቡ ሲጠይቁ ሰዎች መሆናችንን ሁሉ የዘነጉ ይመስሉ ነበር፡፡
መንግሥት የሰላም አማራጮችን ለማየት እና ለጦርነቱ ፖለቲካዊ የሰላም መፍትሔ መንገድ ለመጥረግ ሲል የተሳሳተ ትርክቱ ስትራቴጅስቶች፣ የጦርነቱ ነጋሪት ጎሳሚዎች እና ተሳታፊዎችን ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ እርግጥ ነው በእነዚህ ግለሰቦች ከእስር መለቀቅ መከራ እና ፍዳ ሲያይ የኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጊዜያዊ መደናገጥ እና ቅሬታ ተፈጥሮበታል፡፡ ነገር ግን የትሮይ ፈረሶቹ መደናገጥ የተፈጠረበትን እና ቅሬታ ያደረበትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሞራል መጠበቅ ባይፈልጉ እንኳን መንግሥት ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ የሄደበትን የሰላም ርቀት እውቅና መስጠት እንኳን አልፈለጉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የሰላም ሂደቱ ለሴራዎቻቸው ማርከሻ ከመሆናቸው ባለፈ የግል ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟላ አልነበረምና ነው፡፡
ሌላው ቢቀር እንኳን በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች አሁንም ድረስ በወረራ ስር ናቸው፤ በአፋር የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ በዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው፤ ከ12 ሚሊየን በላይ የአማራ ሕዝብ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ተዳርጓል፤ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ባሉበት እንዲረጉ እና ከግጭት ለመራቅ ወስኗል፤ ይኽን እውነታ ተቀብሎ ዜጎችን ከስቃይ ለመታደግ መፍትሔ ከመሻትና በበጎ ጎኑ ተቀብሎ ከመደገፍ ይልቅ ለሌላ ሴራ እና የእጅ አዙር ጥምዘዛ ላይ ታች ሲሉ ማየት በእጅጉ ያማል፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባላስገባ እና የሚደረገውን የሰላም ጥረት በሚያቀጭጭ መልኩ “HR. 6600 እና S. 3199” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን የማዕቀብ ረቂቅ ሕጎች ለማጽደቅ የሚደረገው ጥረት በእርግጥም ጉዳዩ የፍትሕ፣ የሰብዓዊ እና የዲሞክራሲ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከዚህ የተሻገረ መሻት እንዳለው ያመላክታል ይላሉ በባልሲሊ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር እና በዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምሕርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት አን ፊትዝ ጄራልድ።
የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ሲቪክ ካውንስል ዳይሬክተር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ደግሞ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሀገራትን ሉዓላዊነት ለመድፈር ከመሞከር፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ከማቀጨጭ እና በፍትሕ አደባባይ አድሏዊ አመክንዮ ይዞ መቅረብ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ “የውጫሌ ውል” በምን መልኩ ይለያል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የማዕቀብ ረቂቅ ሕጎቹ የሁለቱን ሀገራት ለዘመናት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስለሚያሻክር የፕሬዚዳንት ባይደን አሥተዳደር ጉዳዩን እንዲያጤነውም ይጠይቃሉ፡፡
ድሃ ሀገራትን ለማንበርከክ፣ የጥቂት ግለሰቦችን ኪስ ለማዳጎስ እና የተወሰኑ ግለሰቦችን የፖለቲካ ፍላጎት ለማርካት ሲባል ብቻ በተጠና፣ በተናበበ እና በታቀደ መልኩ የሚደረግ ዘመቻ እንዴት ራሷን ታላቅ አድርጋ ከምታቀርበው ሀገር የኮንግረስ እና የምክር ቤት አባላት ጓዳ ይጠነሰሳል? ሲሉ የሚጠይቁት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምሕርት ክፍል መምሕር እና እጩ ዶክተር የሆኑት ሙሉነሽ ደሴ ናቸው፡፡ ይኽ የሴራ መንገድ ራሷን የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ ጉዳዮች አልፋ እና ኦሜጋ አድርጋ ለምታቀርብ ሀገር የሚያሳዝን እና የሚያስተዛዝብ ድርጊት ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍር ሩጫም ጭምር ነው ይላሉ መምሕሯ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሯ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት አቋም የተለየ እና ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ልክ እንደ “በቃ” ንቅናቄ ተቃዉሟቸውን በአደባባይ ማሳየት ይኖርባቸዋል ሲሉም አመላክተዋል፡፡
እንደ መምሕር ሙሉነሽ ዕይታ ቀውስ ውስጥ በገባው የዓለም ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ አዙሪት ላይ እንደዚህ ዓይነት አሳሪ የማዕቀብ ሕጎችን ማጽደቅ ይጎዳል፡፡ ማዕቀቡ ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ለመጣል፣ አቅመ ቢስ መንግሥት እና ሀገር ለመገንባት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፤ በመኾኑም ከመጽደቁ በፊት ግንዛቤ መፍጠር የዲፕሎማቶቻችን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተቀዳሚ ተግባር መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያሰማራቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ ብዙ ናቸው፤ ስለሆነም ረቂቅ ሕጎቹ አይጸድቁም ይጸድቃሉ ሳይሆን በመንግሥትም በኩል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/