ʺክርስቲያን በጸሎት ሙስሊም በሶላት፣ እምዬ ኢትዮጵያ የእምነት ባላደራ ደጀ ሰላም ናት”

203

ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እንዳይገፏት ዓለት ላይ የጸናች፣ እንዳይሽሯት በደም ማሕተም የታተመች፣ በአጥንት የጠነከረች፣ በማይበጠስ የምስጢር ገመድ የታሰረች፣ በማይደፈር ጥላ ሥር የተጠለለች፣ ከገዘፉት የገዘፈች፣ ከጠነከሩት የጠነከረች፣ ውዥንብር የማያናውጻት፣ መከራ የማያስደነግጣት፣ ወርቃማው ታሪክ ከፍ አድርጎ የመዘገባት፣ ከነብር የፈጠኑ፣ ከአንበሳ የጀገኑ ጀግኖች የሚጠብቋት ሆነችባቸው፡፡ ሳይቀድሟት የቀደመች፣ ዓለም እንቅልፍ ላይ በነበረችበት ዘመን የተራመደች፣ ጨለማ በበዛበት፣ ስልጣኔ ባልነበረበት በዚያ ዘመን በስልጣኔ የተጓዘች፣ የጨለማውን ዘመን የጣለች፣ ጨለማ ለሆነባቸው ሁሉ ብርሃን የሰጠች፣ የብርሃን መገኛ መንገዱንም ያሳየች እመቤት፡፡
በታሪኳ የሚቀኑት፣ በውስጧ ያለውን የሚያልሙት፣ ስሟን ለማጥፋት የሚፈልጉት ሁሉ በአንድነት መክረውባታል፣ ቢቻለን እናጥፋት፣ ባይቻለን ግን አብረን ተባብረን ቅኝ እንግዛት፣ ሃብቷን እንውሰድባት፣ የሚስጥሯን ሙዳዮች እንበርብርባት፣ ከፍ ያለችውን ዝቅ እናድርጋት፣ በጦርነት እናንበርክካት፣ በግድ እናስገብራት ሲሉ ዶልተዋል፡፡ በምክራቸው መሠረት ጦር አዝምተውባታል፣ በግራም በቀኝም፣ በፊትም በኋላም ወግተዋታል፣ እርሷ ግን ከጠላት ምኞትና ስልት በላይ ናትና በቀኝ ይምጣ በግራ በኋላም ይምጣ በፊት ሁሉንም ድባቅ መትታ መልሳቸዋለች፡፡ ትመልሳቸዋለች፡፡
ብዙ ጊዜ የጥፋት ድግስ ተደግሶባታል፣ ብዙ ጊዜ ሠራዊት ዘምቶባታል፣ ዳሩ የተደገሰውን የጥፋት ድግስ ደጋሹ ይጠጣዋል፣ የዘመተው ሠራዊት ይዞት የመጣው ጠመንጃ ይበላዋል፡፡ ጀግኖች ልጆቿ ጠላትን እየማረኩ፣ በዱር በገደል እያንበረከኩ፣ ድባቅ ይመቱታል እና፡፡ ብዙዎች ይገረሙባታል፣ ብዙዎች ያደንቋታል፣ ብዙዎች በአፈሯ በተፈጠርን፣ የእርሷ ልጅ ባደረገን ይሏታል፡፡ ኃያልነቷ የገባቸው፣ ቀዳሚነቷ የተገለጠላቸው፣ አይነኬነቷ የታወቃቸው የእርሷን እናትነት፣ የእርሷን ቀዳሚነት፣ የእርሷን አሸናፊነት፣ የእርሷን ኃያልነት ይመኛሉ፡፡
ኃያልነቷ ያልተዋጠላቸው፣ በታሪክ መበለጥ የሚያንገበግባቸው፣ ብራና ሲመረመር፣ ምስጢር ሲመሰጤር፣ ታሪክ ሲዘከር በቀዳሚነት መነሳቷ፣ በማያረጀው ብራና፣ በማይጠፋው ቀለም ከፍ ከፍ ማለቷ የሕሊና እረፍት የሚነሳቸው አለመኖሯን ይመኛሉ፡፡ እርሷ ግን ጠላቶቿ በሚያስቡላት መንገድ ተጉዛ አታውቅም፣ የእርሷ ጎዳናዋ እውነት፣ አንድነት፣ አሸናፊነት፣ ጽናት፣ ቀዳሚነት ነው፡፡
እርሷን ከማንም ጋር አታወዳድሯት የሚወዳደራት የለምና፣ እርሷን ከማንም ጋር አታመሳስሏት እርሷን መስሎ የተፈጠረ አይገኝምና ይላሉ አበው፡፡ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ የምትደምቀው፣ በጠበቀ ሃይማኖት፣ ኃያል በሆነ እሴት የምትጠበቀው ኢትዮጵያ ድንቅ ምድር ናት፡፡ በዚህች ታላቅ ሀገር መፈጠር መመረጥ ነው፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄደው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አሸናፊው ተብሎ የሚዘመርለት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ጥቁሮች ተስፋ የሚደርጉት ኢትዮጵያን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ ናትና፡፡
የፈጣሪ ስም ሳይጠራባት፣ አዛን ሳይባልባት፣ ኪዳን ሳይደረስባት፣ ቅዳሴ ሳይቀደስባት፣ ለምድር በረከት፣ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ሳይለመንባት ውላ አታወቅም፡፡ በቀንም ቢሆን በማታ፣ ሳይቋረጥ የፈጣሪ ስም ይመሰገንባታል፡፡ አበው ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት አድርጎ እንዲያኖራት ባለመቋረጥ ተማጽኖ ያቀርባሉ፡፡ ስለ ዓለም ሰላም፣ ስለ ሰው ልጆችም ፍቅር ይለምናሉ፡፡ ፈጣሪም የለመኑትን አይረሳም፣ የጠየቁትን አይነሳም ይሰማቸዋል፡፡
በወላጆቻቸው ጸሎት የሚበረቱት፣ የአባቶቻቸውን ታሪክ የሚያስቀጥሉት፣ በኢትዮጵያ ዳር ድንበር የሚኖሩት ጀግና ልጆቿ ደግሞ ሳያንቀላፉ፣ በተጠንቀቅ የእናታቸውን ክብር ይጠብቃሉ፡፡ ለሚወዷት እናታቸው፣ ለሚምሉላት ሠንደቃቸው፣ ለሚመኩባት ምልክታቸው፣ ለተከበረው ሕዝባቸው ሲሉ ውድ ሕይዎታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ለሠንደቃቸው ክብር፣ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ፍቅር ሲሉ ሞትን ይንቃሉ፣ መቸገረን ይረሳሉ፡፡
መሞታቸው ለክብሯ ነው፣ መቁሰላቸው ለፍቅሯ ነው፣ መራብና መጠማታቸው ለታሪኳ እና ለገናናው ስሟ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ነው የማይደረስበት፣ ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው አምሳያ ያልተገኘለት፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው የሚወዱት የከበሩበት፣ ኢትዮጵያዊነት ጸጋ ነው ብዙዎች ተከብረው የኖሩበት፣ ኢትዮጵያዊነት ኅብረት ነው ጠላትን ድባቅ የሚመቱበት፣ ኢትዮጵያዊነት እሳት ነው ጠላት የሚቃጠልበት፣ ኢትዮጵያዊነት ሰይፍ ነው ጠላት የሚቀሰፍበት፣ ኢትዮጵያዊነት የማያረጅ ካባ ነው የሚያጌጡበት፣ ኢትዮጵያዊነት የፍቅር ጥላ ነው ፍቅር ያጡት የሚጠለሉበት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው በአሸናፊነት የሚኖሩበት፡፡ ኢትዮጵያን ያስከበራት የጸናው ኢትዮጵያዊነት፣ የበረታው አንድነት፣ የጠበቀው እሴት፣ ኃያል የሆነው ሃይማኖት፣ የእናትና አባት ውርስ የሆነው ጀግንነት፣ መገለጫ የሆነው አትንኩኝ ባይነት እና አልሞ ተኳሽነት ነው፡፡
በተከበረችው የኢትዮጵያ ጉያ፣ በተከበረው ኢትዮጵያዊነት እቅፍ ውስጥ የችግር በሮች መክፈቻ ቁልፍ፣ የዘመንን ክፉ ማዕበል መሻገሪያ፣ ከምንም በላይ ከብሮ መከበሪያ አለ፡፡ የጨለመ የሚመስለውን ዘመን ለመሻገር መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ አበው የከፋውን ዘመን የተሻገሩት፣ አይገረሰስም የተባለውን የገረሰሱት፣ ማሸነፍ አይታሰብም የተባለውን ያሸነፉት፣ ሀገራቸውን አስከብረው ተከብረው የኖሩት በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊነት የሚመልሳቸው፣ አንድነት የሚያሸንፋቸው ችግሮች በኢትዮጵያ ላይ ሞልተዋል፡፡ በውስጥ ከእርሷ አብራክ የተገኙ ባንዳዎች፣ ዓላማ ቢሶችና መለያየትን ናፋቂዎች እረፈት ይነሷታል፡፡ በውጭ እኛን ብቻ ስሚን፣ እኛ ብቻ የምንልሽን አክብሪ የሚሉት እያዋከቧት ነው፡፡
የውስጦቹ በብርድና በጸሐይ ተንከራትተው፣ በጭቃና በነዳድ በረሃ ተንገላተው አርሰው፣ አፍሰው፣ አልብሰው፣ አጉርሰው የሚያድሩትን ንፁሃን ገበሬዎች ይገድላሉ፣ ከሞቀ ቤታቸው ያስወጣሉ፣ ሃብትና ንብረታቸውን ይወስዳሉ፣ የተረፈውን ያወድማሉ፡፡ የውጮቹ በሕዝቦቿ ላይ የከፋ ችግር ይመጣ ዘንድ ያለ እረፍት ይሠራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ጠላት አድራ አታውቅም፣ ኢትዮጵያውያን እያሉ ግን ተገፍታ አትወድቅም፡፡ የማያስነኳት ልጆቿ ናቸውና፡፡
የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቱ የተነሱትን የበዙ ጠላቶች ያሸነፉት በአንድነት፣ በጽናት፣ በብልሃት፣ በረቀቀው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የዛሬዎቹን ጠላቶችም ማሸነፍ የሚቻለው በአንድነት፣ በብልሃት፣ በአርቆ አሳቢነት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነትና መበርታት ለጠላቶች ራስ ምታት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን መለያየትና መገፋፋት ደግሞ ለጠላቶቿ ሰርግና ምላሻቸው ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያውያን መከፋፈል ውስጥ የሚሹትን ያገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን መገፋፋት ውስጥ ለዘመናት የተመኙትን፣ ለዘመናት የደከሙበትን ያገኛሉና፡፡
የኢትዮጵያውያን አንድነት ክፍተት ካልተገኘበት የትኛውም ፈተና አቅም የለውም፣ የትኛውም ችግር የኢትዮጵያውያንን ክብር አያጎድለውም፡፡ መድኃኒቱ ያለው ከአንድነት ላይ ነውና፡፡ አንድነትን ማጽናት፣ ኢትዮጵያውያን አማኞች ናቸውና በእምነታቸው መጽናት፡፡ እስከ ሞት ድረስ መታመን ግድ ይላል፡፡
ʺክርስቲያን በጸሎት ሙስሊም በሶላት፣
እምዬ ኢትዮጵያ የእምነት ባላደራ ደጀ ሰላም ናት” እንዳለች ባለ ቅኔዋ ኢትዮጵያ አደራ የሚጣልባት፣ ቃል ኪዳን የማይሻርባት፣ ሃይማኖት የሚጸናባት፣ ጀግና የሚወለድባት፣ ጠላት የሚያፍርባት፣ ኾኖለት የማይኖርባት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም ደጅ ናት እልፎች ሰላም ባጡበት ዘመን ሰላምን የገበዩባት፣ በጨነቃቸው ዘመን እፎይታን ያገኙባት፣ በተከፉበት ዘመን መጽናናትን ያገኙባት ናት፡፡ ጠባቂዋ አያንቀላፋም፡፡ ክርስቲያኖች በጸሎት፣ ሙስሊሞች በሶላት ለሀገራቸው ሰላም ፈጣሪያቸውን ከለመኑ፣ በሀገራቸውም ጉዳይ በአንድነት ከቆሙ ኢትዮጵያን የሚያከብራት ይበዛል እንጂ ኢትዮጵያን የሚደፍራት አይገኝም፡፡ እርሷ የእምነት ባለዳ ናት፤ አደራውንም አትበላም፡፡ ቃሏንም አታጥፍም፡፡ የተሰጣት ቃልም አይታጠፍም፡፡
ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ናት፣ ስርዓት ገፋኝ ብለው የማይገፏት፣ ዘመን ተወኝ ብለው የማይተዋት፣ ሰዎች አስቀየሙኝ ብለው የማይቀየሟት፣ በተቀደሰው ምድሯ የሚኖሩባት፣ በደስታ የሚያድጉባት፣ በክብር የሚኖሩባት፣ በኋለኛው ዘመንም በአፈሯ የሚያርፉባት ረቂቅ ናት፡፡ እርሷን ከማንም ጋር አታወዳድሯት፣ ለውድድርና ለንጽጽር የማትቀርብ ልዩ ናትና፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleቺርቤዋ፡- ሜጋቢት 15/07/2014 ም.አ (አሚኮ)
Next articleኤች.አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን ለማስቆም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡