
አሁን የፀጥታ አካላት ሁኔታውን አረጋግተዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ አካባቢ በግለሰቦች የዕለት ግጭት የተነሳ የፀጥታ መደፍረስ ለሰው ህይዎትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማቻ፣ አምቦበር ውዛባ እና ቡርቧክስ በተባሉ ቀበሌዎች ነው የፀጥታ መደፍረስ የተከሰተው።
በዞኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ጌትነት አልታሰብ ለአብመድ እንደተናገሩት ትናንት ማቻ ቀበሌ ላይ በግለሰቦች መካከል ግጭት ተከስቶ ነበር፤ ይህን ተከትሎም ቤቶች ተቃጥለዋል፤ በሌሎች ንብረቶች ላይም ጉዳት ደርሷል።
እንደ ኮማንደር ጌትነት መረጃ የፀጥታ አካላት ጉዳዩን አረጋግተው ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ጥቅምት 3/2012 ዓ.ም ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በመጀመሪያ አምቦበር ውዛባ ላይ፣ ቀጥሎም ቡርቧክስ በተባለ ቀበሌ በተለያዩ ሰዓታት የፀጥታ መደፍረስ ተከስቶ ነበር። በሁለቱም ቀበሌዎች ቤቶች መቃጠላቸውም ታውቋል።
የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት፣ የአካባቢው ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት በሁሉም አካባቢዎች ሁኔታዎቹን ማረጋጋታቸውን ያስታወቁት ኮማንደር ጌትነት ስለ ወደመው የንብረት መጠን የተጣራ መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልፀዋል። በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንጂ ምን ያህል ለሚለው ጥያቄ የተጠናቀረ መረጃ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት።
በተያያዘ ዜና በጎንደር ከተማ አካባቢ ጠዳ፣ ምንዝሮ፣ ፈንጠር እና አየር ጤና አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ ተከስቶ እንደነበረ ታውቋል። የጸጥታ ኃይሎች ሁኔታውን በመቆጣጠር አካባቢውን ማረጋጋታቸውንም ፖሊስ አስታውቋል።
በተፈጠረው ችግርም የሰው ህይወት ማለፉን፣ የመቁሰል አደጋ መድረሱን፣ የቤት ቃጠሎ እና የንብረት ውድመትም መከሰቱን ነው ፖሊስ ለአብመድ የገለፀው።
በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው የአደጋ መጠን እየተጣራ እንደሆነም ታውቋል።
በጎንደር ዙሪያም ይሁን በጎንደር ከተማ አካባቢ የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች ከዚህ ቀደም ከነበረው ችግር ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውም ፖሊስ አስታውቋል።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ