
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሕዝብ የሽምግልና ሥርዓት ማኀበር የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች የገጠማቸውን የርሃብ አደጋ ለመታደግ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሊደግፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
ድጋፉ የሚሰባሰበው “የጾም ቁርሳችን ለተራቡ ወገኖቻችን” በሚል መሪ ሐሳብ ነው።
በአሁኑ ወቅት የዐቢይ ጾም እየተጾመ እና የረመዳን ጾምም እየተቃረበ በመኾኑ አጿማቱን ምክንያት በማድረግ የሃይማኖቶቹ ተከታዮች ለርሃብ ተጋላጭ ለኾኑት ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ማኅበሩ ጥሪ አስተላልፏል።
የሕይወት አድን ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሕዝብ የሽምግልና ሥርዓት ማኀበር ፕሬዚዳንት ሊቀኅሩያን በላይ መኮንን የሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች በቀን 15 ብርና ከዚያ በላይ በመቆጠብ በቅርቡ ለድጋፉ በሚከፈተው የባንክ የሒሳብ ቁጥር ገቢ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ገለጻ ድጋፍ ማድረግ ታላቅ የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ በመኾኑ የእምነቱ ተከታዮች እጃቸውን ሊዘረጉ ይገባል።
የእምነቶቹ ተከታዮች ከዛሬ ጀምሮ ለድጋፉ መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። አጽዋማቱን ተከትሎ በሚከበሩ በዓላት የተራቡ ወገኖችን ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በሰርግ፣ በተስካርም ኾነ በተለያዩ ድግሶች የተራቡና የታረዙ ወገኖችን ማሰብ ቅድሚያ እንዲሰጠውም አስገንዝበዋል።
የሚሰበሰበው ድጋፍ የሚውለው የአፋር ክልልንም ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ለተጎዱ ወገኖች እንደኾነ የጠቆሙት ሊቀኅሩያን በላይ የሃይማኖት አባቶችም ሥራው የተሳካ እንዲኾን ሕዝባቸውን ሊያስተምሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ሸህ ከድር ያሲን እንዳሉት የረመዳን ወር ታላቅ ወር በመኾኑ እምነቱ እንደሚያዘው ያለንን ለድሆች ማካፈል ያስፈልጋል። እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ሃይማኖት ተከታይ ለተራቡ ወገኖች እጅን መዘርጋት ይጠበቃል ነው ያሉት።
በቅዱስ ቁርዓን ትዕዛዝ ያለው ለሌለው ድጋፍ ማድረግ ሃይማኖቱ የሚያስገድድ መኾኑን አስገንዝበዋል። የተራበን ማብላት፣ የታረዘን ማልበስ ከአላህ ዘንድ በጀነት ታላቅ ደስታን ያስገኛል ብለዋል።
የሚከፈተው የባንክ የሒሳብ ቁጥር በክልሉ መንግሥት እውቅና ያለውና ሕጋዊ እንደሚኾንም ማኅበሩ አስታውቋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/