ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄዱ ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያካሂዱ ቦርዱ አሳሰበ።

109

ለፓርቲዎች የሚደረገው የ50 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ቀመር ወጥቷል።

መጋቢት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በመከረበት ወቅት እስካሁን ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄዱ ፓርቲዎች በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዲያካሂዱ እና መተዳደሪያ ደንባቸውን እንዲያሻሽሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አሳስበዋል።

26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ እንዳለባቸው ቦርዱ በደብዳቤ አሳውቋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ያላካሄዱ መኖራቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል። ጉባዔ ያላካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ አካሂደው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

መተዳደሪያ ደንባቸውን እንዲያሻሽሉ የተሰጠው ደብዳቤ አፈጻጸም ላይ በሚገባ ተፈጻሚ እየኾነ አይደለም ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ጠቅላላ ጉባዔ ያላደረጉ ፓርቲዎች ከሕጉም ኾነ ከመመሪያው አንጻር መተዳደሪያ ደንብ በሚያሻሽሉበት ጊዜ ከሕጉ ጋር ሳይጣረስ መፈጸሙንም ማየት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ፊት ሰፊ ውይይት እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

ፓርቲዎች በሚያደርጉት የጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቦርዱ ታዛቢዎች ኹሉንም ሂደት መያዝ እንዲችሉ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል። በዚህ ረገድ ከአሁን ቀደም ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄዱ አንዳንድ ፓርቲዎች ትብብር አለማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የበጀት ድጋፍን በተመለከተ ቦርዱ ለተጨማሪ በጀት 230 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፤ ነገር ግን ሀገሪቷ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ይህ ገንዘብ እንደማይፈቀድ ምላሽ እንደተሰጠው አንስተዋል።

መንግሥት ለምርጫው የወረቀት ሕትመት ከሰጠው ብር ተመላሽ የኾነውን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንዲደረግ ቦርዱ ያስፈቀደ ሲኾን፤ በዚህም ወደ 50 ሚሊዮን ብር ገዳማ በእኩልነትና ፓርቲዎች በሰጡት መረጃ እንዲሁም ከቦርዱ የተገኙ ሰነዶችን ታሳቢ በማድረግ ክፍፍል እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ከሚመደበው በጀት 30 በመቶ ለሀገራዊ ፓርቲዎች፤ 20 በመቶ ለክልላዊ ፓርቲዎች ሌሎች ደግሞ ከሴት አባላት ብዛትና በሴት አመራር አባላት ብዛት እንዲሁም በአካል ጉዳተኛ አመራርና አባላት ብዛት በሚል ነጥብ የሚሰጥ እንደኾነ አመላክተዋል።

ከድልድሉ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ፓርቲዎች ቅሬታ ያቀረቡ ሲኾን አሠራሩ ሕግን ተከትሎ የተፈጸመ ስለመኾኑ ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።

በመድረኩ ቦርዱ ፓርቲዎች ያቀረቡትን አቤቱታዎች መነሻ አድርጎ «ችግር ተፈጥሯል» በተባለባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ምርመራ አድርጎ ተገቢው ሕጋዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ማድረጉን በሪፖርት አቅርቧል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቦርድ እየከፈለ ያለው ዋጋ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው ላይ እንግልት እየተፈጸመ ስለመኾኑ፤ እንደልብ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉና ሌሎች አሉታዊ ተጽእኖዎች እየደረሱባቸው እንዳለ የገለጹ ሲኾን፤ ቦርዱ ዝርዝር መረጃው ቀርቦለት አቤቱታቸውን መነሻ አድርጎ በቀጣይ የማጣራት ሥራውን እንደሚያከናውን ተገልጿል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም ፓርቲዎች ያገኟቸውን የገንዘብ ድጋፍ በትክክል ስለመጠቀማቸው የሚያሳይ የኦዲት ሪፖርት ካልቀረበ የዘንድሮ የገንዘብ ድጋፍ ገቢ መኾን እንደማይችልም ነው ሰብሳቢዋ የጠቆሙት።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል የሚቻለው የንግድ ሥርዓቱ ሲዘምን ብቻ ነው” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
Next articleለአማራ እና ለአፋር ክልሎች ገቢዎች ቢሮ ከ17 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ።