አልማ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ በክልሉ ሰብዓዊ ልማት ላይ አተኩሮ ሊሠራ ነው፡፡

918

የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ጠቅላላ ጉባኤውን በባሕር ዳር እያካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው የአልማ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደርበው ማኅበሩ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሦስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ የለውጥ ዕቅድ ትግባራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕዝባዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት ከ2012 እስከ 2014›› በሚል መሪ ሐሳብ ክልላዊ እና ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

በለውጥ ዕቅዱ በማኅበሩ የተቀረፁ የልማት ዕቅዶችን ለመፈፀም የአልማን አቅም ማሳደግ ቀዳሚ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው 16 በመቶ የሚሆነውን ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች 50 በመቶ እንዲደርሱ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

የማኅበሩን ዘላቂ የገቢ ምንጮች በአዳዲስ ፍኖተ ካርታዎች ማጠናከር፣ የወጣቶችን የሙያ ስልጠናና የሥራ ዕድል ማስፋት፣ በተጠናከረ ካፒታል አዋጭ ፕሮጀክቶች በተጠና አሠራር መተግበር እና ዘጠኝ አዳዲስ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሦስት የለውጥ ዓመታት አልማ ከማኅበሩ፣ ከደጋፊዎች እና ከመንግሥት 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ 24 በአዲስ ሞዴል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ከክፍል ውስጥ እና ውጭ አስፈላጊ ግብዓቶችን ያሟላል፡፡ 415 አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ ከሦስት ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ የተሟላ የደረጃ ማሻሻያ ያደርጋል፤ ከሦስት ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ገመድ አልባ ዲጂታል ቤተ መጽሕፍት ግንባታ ያካሄዳል፡፡

240 አዲስ ግንባታ፣ 41 ቤተ መጻሕፍት፣ 157 ቤተ-ሙከራ፣ 600 ገመድ አልባ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመሥራት ዕቅድ ይዟል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ከሁሉም የክልል ወረዳዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተደረገው ውይይት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፍ ባለ የአማራ ሥነ ልቦና የተበታተነ አቅምን አሰባስቦ ለችግር መፍቻ ለመጠቀም አልማ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

የሁሉንም አባላት ርብርብ የሚጠይቀው የሦስት ዓመታት የለውጥ ዕቅዱ የትምህርት ቤቶችን እና የጤናውን ዘርፍ በማሻሻል ትውልድን ለመገንባት ትልቅ ሚና የሚጫወት ይሆናልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

‹‹የዕቅዱ የመጀመሪያ የሙከራ ሥራውን የምሥራቅ በለሳ ጎሃላ ትምህርት ቤትን ግንባታ በሦስት ወር ውስጥ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ማስገባት ችሏል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ማኅበሩን ወደ ዘላቂ የልማት ግቦች በማሸጋገር የጋራ ችግሮችን እንዲቀርፍ መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አቶ ተመስገን መላው የአማራ ሕዝብ፣ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች እና የልማት ማኅበሩ አጋሮች ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን አሻራቸውን እንዲያሳርፉም አሳስበዋል፡፡

ከአራት ሚሊዮን በላይ በጎ አድራጊ ዜጎችን ያቀፈውን አልማ ለመደገፍ ከዱባይ ባሕር ዳር የተገኙት አቶ ደመቀ ተስፋው ‹‹ዲያስፖራውን ተሳታፊ ለማድረግ እና ስለሚደርገው ድጋፍ መረጃ እንዲኖረው መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

‹‹አልማ ከአባላቱ የሚያገኘውን ውስን ሀብት ትልልቅ ችግሮቻችን እንዲፈቱ በማድረጉ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡ ቀጣይ በሚኖረው የለውጥ ዕቅድም ሰፊው ዲያስፖራ ተሳታፊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ከእያንዳንዱ ግለሰብ የሚዋጣው የአባልነት መዋጮ ሰብዓዊ ልማቶችን በመገንባት የነገን ችግሮች ከመቅረፍ በላይ የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ አልማ በክልሉ ትምህርት እና ጤና ዘርፍ የሚያደርገው ርብርብ ለሁሉም ዜጎች ተጠቃሚነት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ዛሬ ተጀምሯል። 
Next articleየግለሰቦች ግጭት ህልፈተ ህይዎትና የንብረት ጉዳት አስከተለ።