
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የቆየው የሀገሪቱ የንግድ ሕግ ባለፈው ዓመት ተሻሽሏል፡፡ ሦስት የተለያየ ርእዮተ ዓለማዊ ዕይታ የነበራቸውን መንግሥታት ያሳለፈው የንግድ ሕጉ ዘመኑን በዋጀ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተሻሽሏል ነው የተባለው፡፡
በሌላ በኩል ከመጭው ሐምሌ ወር ጀምሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው ተብሏል፡፡ በሁለቱ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በየደረጃው ለሚገኙ የዘርፉ የሥራ ኅላፊዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡
ላለፉት ሥድሳ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የንግድ ሕግ ዘመኑን በዋጀ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ተሻሽሏል ያሉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሃመድ ናቸው፡፡ የተሻሻለው የንግድ ሕግ የዓለም አቀፉን የንግድ ሕግ የተከተለ ነው ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂ፣ አዳዲስ አሠራሮች፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እና የመረጃ አሰጣጥ ስርዓትን ማሻሻል እድሜ ጠገቡን አዋጅ ለማሻሻል ምክንያቶች ነበሩ ተብሏል፡፡
የቀድሞው ንግድ ሕግ እጅግ ጠንካራ መሰረት ያለው እና ዘመናትን አሻግሮ ያየምና የተሻሻለው የንግድ ሕግም ተጨማሪ እሳቤዎችን እና የተቀየረውን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡ “ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል የሚቻለው የንግድ ሥርዓቱ ሲዘምን ብቻ ነው” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን ደግሞ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የንግድ ሥርዓቱ ከተለመደው ውስብስብ፣ ጊዜ አባካኝ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ምንጭ እንዲጸዳ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ከመጭው ሐምሌ ወር ጀምሮ በኦላይን (በይነ መረብ) ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በኩል እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀሰን በጦርነቱ ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እና ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሠራር በየደረጃው እየተዘረጋ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኅላፊ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ናቸው፡፡ የንግድ ሕጉ መሻሻሉ እና የኦላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መጀመሩ ለሂደቱ አመላካቾች ናቸው ብለዋል፡፡
የንግድ ሕጉን በየደረጃው ለሚገኘው ፈጻሚ እና አስፈጻሚ አካላት ለማድረስ የአሠልጣኞች ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል አቶ ቀለመወርቅ፡፡ በቀጣይም ያልተቋረጠ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የአሠራር ሥርዓቶቹን የማስረጽ እና የተሻሻለውን ሕግ የማስተዋወቅ ሥራዎች ይከናወናሉም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/