ሕፃናት እና እናቶች አኹንም የኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ ይሻሉ።

211

ሰቆጣ: መጋቢት 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የሕፃናትና እናቶች የጤና ኹኔታ አሳስቦኛል ብሏል። የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ እንዳሉት ጤና መምሪያው የተፈናቀሉ እናቶች እና ሕፃናትን በየሳምንቱ የሥነ ምግብ ልየታ ያደርጋል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሚገኙ አራት የተፈናይ መጠለያ ጣብያዎች በተደረገው ልየታም እናቶች እና ሕፃናት ለከፋ የምግብ ችግር መጋለጣቸው ተረጋግጧል።

ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት እድሜ ክልል ከሚገኙ ሕፃናት ውስጥ ከ700 በላይ ሕፃናት መካከለኛ እና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለባቸው ናቸው ብሏል ጤና መምሪያው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 4 ነጥብ 4 በመቶ የሚኾኑት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለባቸው ናቸው። በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ያለፈ ሕፃናት መኖራቸውንም ኀላፊው አንስተዋል። በመጠለያ ጣብያዎቹ ከሚገኙት 700 የሚጠጉ አጥቢ እና ነፍሰጡር እናቶች ውስጥ 80 በመቶ ገደማ የሚኾኑት መካከለኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

የምግብ እጥረት ያጋጠማቸውን ሕፃናት እና እናቶች የጤና ኹኔታ ተፈናቅለው በመምጣታቸው የችግሩን ክብደት ማወቅ ተቻለ እንጂ በጠላት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ወረዳዎች የሚኖሩ ሕፃናት እና እናቶች ያሉበት ኹኔታ ከዚህም በላይ ሊከፋ እንደሚችል አቶ አሰፋ ገልጸዋል። ጤና መምሪያውም ከአቅሙ በላይ በመኾኑ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ መቸገሩን ነው ኀላፊው የገለጹት።

የምግብ ችግር ላጋጠማቸው እናቶች እና ሕፃናት ድጋፍ እንዲያደርጉ የተጠየቁ የመንግሥት ተቋማት እና ረጂ ድርጅቶች በቂ ምላሽ አለመሥጠታቸው ችግሩን የተወሳሰበ አድርጎታል። ቀይ መስቀል ጥናት ከማድረግ ውጭ ምን አይነት ግኝት እንዳገኘ እንኳ ማወቅ አለመቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

ጤና መምሪያውም በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተወሳሰበ ችግር ያጋጠማቸውን ሕፃናት ባለው አቅም ልክ ሕክምና እየሰጠ ቢገኝም የአስታማሚዎች የምገባ ኹኔታ ሌላው ትልቅ ፈተና እንደኾነ ነግረውናል።

ረጅ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማት እና ሰብዓዊነት የሚሰማው ማንኛውም አካል አስቸኳይ የኾነ የእለት ምግብ፣ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የመጸዳጃ፣ የሕክምና እና ሌሎች አቅርቦቶችን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል። በተለይም ደግሞ ክልሉ ለችግሩ ክብደት ትኩረት ሰጥቶ ትላልቅ አቅም ያላቸውን ፕሮጀክቶች ወደ አካባቢው እንዲያስገባ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በበኩላቸው በቀጣናው ያላውን የጤና ሁኔታ በየጊዜው እየተገመገመ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት የእናቶች እና ሕፃናት የጤና ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ የሚኾንበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጸው የሚቀርቡ ግብዓቶችን በተገቢው መንገድ ማሰራጨት ከተቻለ ችግሩን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ አቶ በላይ ወደፊት የተፈናቃይ ቁጥሩ የሚጨምር ከኾነ ችግሩ ከፍ ሊል እደሚችል ታውቆ ሁሉም የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleዜና መጽሔት ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
Next articleየአማራ ክልል ግብርናና አግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች ገበያ መዳረሻ ድርጅት የገበያ ክፍተትን ለመሙላትን ለማረጋጋት የሚያከናውናቸው ተግባራትን መደገፍ እንደሚገባ የክልሉ ንግድ ቢሮ ኀላፊ ቀለመወርቅ ምህረቴ ገለጹ፡፡