
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መኖር ባለመኖር ውስጥ እያለ፣ ሰማይ ሳይዘረጋ ምድር ሳትጸና፣ የንፋስ አውታሮች ሳይነፍሱ፣ ቀላያት ሳይፈስሱ፣ የሚታየውና የማይታየው ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቆጠር አስቀድሞ ይኖር ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ ኖረ፣ እስከዚህ ዘመንም ይኖራል አይባልም፡፡ እርሱ ዘመን የማይቆጠርለት፣ መንግሥቱ ሽረት የሌለበት፣ ረቂቅነቱ ተመርምሮ የማይደረስበት ኃያል ነውና፡፡
ዓለማት ሳይፈጠሩ፣ ምድርና ሰማያት ሳይኖሩ፣ አዕዋፋት ሳይበሩ፣ መላእክት ለአገልግሎት ሳይፋጠኑ እርሱ ይኖር ነበር፡፡ ከዓለማት በፊት የነበረው፣ በዓለማት መካከል ያለው፣ ከዓለማት ማለፍ በኋላ የሚኖረው፣ ሕያው የሆነ ጌታ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣት፣ ክብሩን እና ልእልናውን ገለጠባት፣ ረቂቅነቱን አሳየባት፡፡ ፍጥረታትን ፈጥሮ በተዘጋጀላቸው ሥፍራ አስቀመጣቸው፡፡ ለሰው ልጅም የተቀደሰችውን ሥፍራ ይኖርባት ዘነድ ፈቀደለት፡፡ የሰው ልጅ ግን ትዕዛዙን ተላለፈ፣ ወሰኑን አለፈ፡፡ በጥፋቱም ተቀጣ፡፡
ብርሃን የመላበት ክብሩ ሲገፈፍበት፣ ዙሪያውን ጨለማ ሲበዛበት፣ ቅዱስ መንፍስ ሲርቀው፣ እርኩስ መንፈስ ሲቀርበው በጥፋቱ ተጸጸተ፡፡ አብዝቶ አለቀሰ፡፡ ጌታም ለቅሶውን ሰምቶ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ ተበድሎ ሳለ ራሱ ሊክስ፣ ስጋውን ሊቆርስ፣ ደሙን ሊያፈስስ ቃል ገባለት፡፡ ቃሉ የማያልፈው አምላክ በቃሉ መሠረት ሰውን ሊያድን መጣ፡፡ በምድርም ተመላለሰ፡፡ አስቀድሞ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ልጅ ወደ ክብሩ መለሰው፣ የማያልፈውን፣ የማይቀደደውን፣ የማያረጀውን የክብር ካባ አለበሰው፡፡
ደቀመዛሙርቱ፣ ጸሐይ የሚያንጸባርቅበትን፣ ግንቡ ያማረውን አብዝቶ የተዋበውን ቤተ መቅደስ አይተው ተደነቁ፡፡ እነርሱ የተደነቁበትን ቤተ መቅደስ ያሳዩት ዘንድ ወደዱ፡፡ ቀረቡም፡፡ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ ንፍቅ በሚገኘው፣ የወይራ ዛፍ በሚበዛበት ተራራ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ በምድር ላይ አስቀድመው የተመረጡ፣ ምስጢር የተገለጠባቸው፣ ማዳን የታየባቸው ተራራዎች አሉ፡፡ ታቦተ ጽዮንን ወይም ጽላተ ሙሴን የሰጠባት የሲና ተራራ፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠባት የደብረ ታቦር ተራራ፣ ዓለምን ሊያሳልፍ እንደሚመጣ የተናገረባት የደብረ ዘይት ተራራ አስቀድመው ከተመረጡት፣ ከተባረኩት፣ ከተቀደሱት ተራራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በቅድስቲቷ ከተማ በኢየሩሳሌም በምሥራቅ ንፍቅ፣ በቄድሮን ሸለቆ አጠገብ ይገኛል፡፡ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ እንደሚመጣ የተናገረበት፣ ታላቅ ነገርን ያስቀመጠበት ደብረ ዘይት ተራራ፡፡
ʺኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፡፡ ….. ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” እንዳለ መጽሐፍ ለደቀመዛሙርቱ ታላቁን ቃል ነገራቸው፡፡ ቃሉ አያልፍምና ሰዎች ሁሉ ቃሉን እንዲያከብሩ፣ በቃሉ ውስጥ እንዲኖሩ አዘዘ፡፡ ከቃሉ የወጣ ይቀጣልና፡፡
የሚያብለጨልጩት፣ በምድር ላይ ያማሩና የተዋቡ የሆኑት ያልፋሉ፣ ሀብትም ቢሆን ያልፋል፣ ውበትም ቢሆን ይረግፋል፣ ጉልበትም ቢሆን ይደክማል፣ አጃቢም ቢሆን ይከዳል፡፡ ሁሉም እንዳልነበር ይሆናል፡፡ አብሮ የሚኖረው ወደ ማያልፈው ዓለም የሚያሻግረው ግን እውነት፣ ጽናት፣ ትዕግስት፣ ፍቅር፣ ለሰዎች የሚሰጥ ክብር ነው፡፡
ʺስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።
እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” እንዳለ መቼ እንደሚያልፍ፣ መቼ እንደሚወሰድ የሚያልፍ የለም፡፡ ሁሉም ያልፋሉ፣ ሁሉም ይጠፋሉ፣ የማለፊያ ዘመን እስኪደርስ ድረስ ግን ተዘጋጅተህ ጠብቅ፡፡
ክርስቲያኖች አብዝተው ከሚያከብሩት፣ በጽሞና ከሚፆሙት አጽዋማት መካከል አንደኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡ ይህን ጾም በሱባኤ ጀምረው በትንሳዔው በዓል ይፈጽሙታል፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ሳምንታቱ ትርጓሜ ያላቸው፣ ምስጢራት የበዙባቸው፣ ቤተክርስቲያን በጽናት የምታስተምራቸው፣ ክርስቲያኖችም የሚያስቧቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምስጢራዊ ሳምንታት መካከል አንደኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ነው፡፡ በዚህ ቀን ምጽዓት የሚታሰብበት፣ ምስጢራት የሚመሰጤሩበት ነው፡፡
እነሆ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ምጽዓቱን በማሰብ የምትከበረው፣ ስሟ ከፍ የሚለው፣ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ቃል የሚመሰጤርበት ያቺ ቀን ዛሬ ናት፡፡ በበዓለ ደብረ ዘይት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገደማትና አድባራት ሊቃውንት የምጽዓቱን ቀን ይናገራሉ፣ ምዕምናን የተዘጋጁ ይሆኑ ዘንድ ያስተምራሉ፡፡ ምዕምናንም በበዓለ ደብረ ዘይት በማለዳ ተነስተው ወደ ቤተ መቅደስ ያቀናሉ፡፡ በረከትና ጸጋንም ይቀበላሉ፡፡
በደብረ ዘይት የተናገረው ቃል ሲፈጸም ዓለም እንዳልነበረች ትሆናለች፡፡ የምታሳሳ የምትመስለው፣ ጽኑ እና የማትናወጽ የምትመስለው ባዶ ትሆናለች፡፡ በፈጠራት ኃይል ታልፋለች፡፡ ያን ጊዜ የሚያስፈራው ድምጽ ይሰማል፣ ያን ጊዜ ድንጋጤ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ ፍርድ ይሰጣል፡፡ ሰውም በሥራው ልክ ያገኛል፡፡ በሚያልፈው ዓለም ያደረገውን ሁሉ በዚያች በእለተ ምጽዓት ያገኛታል፡፡ ደጎች እንደ ደግነታቸው፣ ክፉዎችም እንደ ክፋታቸው መጠን ይቀበላሉ፡፡ በሚያልፈው ዓለም የማያልፈውን አድርግ፡፡ መልካሙን ነገር ተከተለው፣ ክፉውን ነገር ከእጅህ ጣለው፣ ከዓዕምሮው አስወጣው፣ ከሀሳብህ ርሳው፡፡ መልካም የሚያደርጉትን ጉርምርምታ አያስደነግጣቸውም፣ ጨለማ አያስፈራቸውም፣ ሞት አያሰጋቸውም፣ ሁሉንም በመልካምነታቸው ያሸንፉታልና የሚያሰጋቸው የለም፡፡ የተዘጋጀህ ትሆን ዘንድ የተቸገሩትን ደግፋቸው፣ ያዘኑትን አጽናናቸው፣ የተራቡትን አጉርሳቸው፣ የተጠሙትን አጠጣቸው፣ የታረዙትን አልብሳቸው፣ የታሰሩትን ጠይቃቸው፣ የተጣሉትን አስታርቃቸው፡፡ ይህን ካደረክ የምጽዓት ጊዜ አያስፈራህም፣ ንውጽውጽታው አያስደነግጥም፡፡ ለምን ካልክ ደግ አድርገሃልና በቀኙ ትቆማለህ፡፡
የተጣሉት በዝተዋል፣ የሚያጣሉት በርክተዋል እና የተጣሉትን አስታርቃቸው፣ የሚያጣሉትን ምከራቸው፣ እምቢ ካሉ ግን ከሃሳባቸው ራቃቸው፡፡ ʺሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም” ያለው ጌታ በደብረ ዘይት የተናገረውን እያሰብክ በምድር ሰላም፣ በረከት፣ ፍቅርና አንድነት ይኖር ዘንድ ጸልይ፡፡ የተስፋዋ ምድር ኢትዮጵያ ሰላሟ እንዲበዛ፣ አንድነቷ እንዲጠነክር፣ ሰው ለሰው መድኃኒቱ እንዲሆን ተማጸን፡፡
ክርስቲያኖች ምጽዓቱን የተናገረበትን ቀን እያሰቡ ትንሳኤውን ያደረገበትን ቀን ይጠብቃሉ፡፡ ጾሙን በጥሞና ያሳልፋሉ፣ በበዓለ ትንሳኤው ደግሞ እልል ይላሉ፡፡ በትንሳኤው ቀን ጌታ ተነስቷል፣ ብርሃን በርቷል፣ የታሰረው ተፈትቷል፣ የክፋት ግንብ ፈራርሷል፣ የሰው ልጅ ወደ ቀደ ክብሩ ተመልሷልና፡፡ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በመጠለያ ውስጥ ያሉትን አስቧቸው፣ የተቸገሩትን እርዷቸው፣ ያዘኑትን አጽናኗቸው፡፡ መንገዳችሁንም አብጁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/