“የጎንደር ሕዝብ ተራ የኾነ ፓለቲካ ውስጥ ገብቶ ከአማራነትና ከኢትዮጵያዊነቱ ማማ አይወርድም” የጎንደር የሰላም እና የዕድገት ማኅበር ጉባኤ ተሳታፊዎች

167

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር የሰላም እና የዕድገት ማኅበር (ጎሰማ) “አብሮነት ለውስጥ ጥንካሬ፤ የውስጥ ጥንካሬ ለሰላምና ለልማት፤ ሰላምና ልማት ለሀገር ህልውና” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ የሰላምና የእድገት ጉባኤ አካሂዷል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ በላቸው ማኅበሩ ለጎንደር ብሎም ለአማራና ለመላው ኢትዮጵያዊያን እህትና ወንድሞቹ ዘላቂ ሰላምና እድገት የበኩሉን ሚና ለመጫወት ሕጋዊ እውቅና ኖሮት የተቋቋመ ሲቪክ ማኅበር ነው ብለዋል። ጎንደርና አካባቢው እምቅ የኾነ ሀብት ስላለው የአካባቢውን ሰላም በማሥጠበቅ ጎንደር እንዲለማና ለአማራ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ አቅም እንዲኾን ማኅበሩ ከሕዝቡ ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ‟ጎንደሬነት በኢትዮጵያዊነት ጽኑ መሠረት ላይ የቆመ መኾኑን አውቀን ከአሁን በኋላ መሳሪያ አንግቦ ሀገርን ከጠላት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በልማትም ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን እንሠራለን” ብለዋል።

ልማትን ለማምጣት ቀዳሚው ነገር ሰላምን ማስፈን ነው ያሉት ተሳታፊዎች ከሌሎች የአማራ ክልልና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ጋር በአንድነት እንደሚቆሙም አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ሕዝብ ለዘመናት ይዞት የቆየውን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል ተጠቅሞ አካባቢውን፣ ክልሉን እና ኢትዮጵያን እንደሚያለማ ነው የጉባኤው ተሳታፊወች የገለጹት።

‘የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው’ ያለው የጎንደር ሕዝብ ተራ የኾነ ፓለቲካ ውስጥ ገብቶ ከአማራነትና ከኢትዮጵያዊነቱ ማማ አይወርድም ያሉት ተሳታፊዎች እንደቀደምት አያትና ቅድመ-አያቶቹ በጥንካሬና በጥበብ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት እንደሚቆሙም አስረድተዋል።

በጎንደር አካባቢ እምቅ ሊለማ የሚችል የሐብት ክምችት አለ ያሉት ተሳታፊዎች ይህንን ወደ ሥራ አስገብቶ ጎንደርን በማልማት ለክልሉ እና ለሀገር ልማት አለኝታ መኾን እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ተሳታፊዎቹ ጎንደሬ ከኾነው የቅማንት ወንድም ሕዝብ ጋር በአንድነት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ወንድም ከኾነው የቅማንት ሕዝብ ጋር ለመነጣጠል የመጣን ጠላት እና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተነሳን ቡድን ዛሬም እንደጥንቱ እንደሚታገሉት የጉባኤው ተሳታፊዎች ገልጸው “ለኢትዮጵያ ዘመናዊነትን እና እድገትን ይዞ ለሚመጣ ጎንደሬወች ሙክት አርደን እንቀበለዋለን” ብለዋል።

የጉባዔው ተሳታፊ ምሁራንም የጎንደር ጥንካሬ ለአማራና ለኢትዮጵያ ጥንካሬ አስተዋጽኦ እንዳለው ሁሉ ድክመቱም ለክልሉና ለሀገር ስለሚተርፍ በሰላምና በልማት ጠንካራ አካባቢን በመፍጠር ለሀገርና ለህዝብ የላቀ አበርክቶ ለማድረግ እንደሚሠሩም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡-አሚናዳብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኢኮኖሚውን ማሳደግ አስፈላጊ መኾኑን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር ) ተናገሩ።
Next article“ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያውያንና ምሥራቅ አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም የተዘጋጀ ነው” ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ