
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለምአቀፉ የሴቶች ቀን በአማራ ክልል “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።
የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት እና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ ኢኮኖሚውን ማሳደግ አስፈላጊ መኾኑን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር ) ተናግረዋል። ርእሰ መስተዳድሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በዓለም ለ111ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ፣ በአማራ ክልል ለ26 ጊዜ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እና ከችግር እንዲላቀቁ ማስተማር ተገቢ ነውም ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።
ሴቶች በትምህርታቸው ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እየኾኑ ነው፤ ይኽን በዘላቂነት ለማስቀጠል ወንዶችም የራሳቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ በበኩላቸው ሴቶች ከደጀንነት ባሻገር በአውደ ውጊያ በመሳተፍ የአካል እና የሕይወት መስዋእትነት ከፍለዋል ለዚኽም ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
ቢሮው ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረጉንም ወይዘሮ አስናቁ ተናግረዋል።
የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቀኑን ከማክበር በዘለለ ሴቶችን ማዕከል ያደረገ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በመርሃ ግብሩ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና በአውደ ውጊያ ለተሳተፉ ሴቶች የምስጋናና የእውቅና መርኃ ግብር እንዳለም ለማወቅ ተችሏል።
በበዓሉ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር )፣ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንንን ጨምሮ የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የወረዳ እና የዞን የሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/