
መጋቢት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረንሳይ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ።
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር የኾነችው ፈረንሳይ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ በተጨባጭ አጋርነቷን ማሳየቷን አውስተዋል።
ሀገራቸው ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመኾን በአማራ፣ በትግራይ፣ አፋር እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪ ፈረንሳይ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም ሀገራቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን የደሴ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሠራች መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት በፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያ ስድስት ወራት 10 ሚሊዮን ዩሮ ለመልሶ ማቋቋምና ምግብ ዋስትና ፕሮጀክቶች የሚውል ገንዘብ መድቦ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ፈረንሳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማስፈን የወሰዳችው እርምጃዎችን እንደምታደንቅም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ ሲወስን ፈረንሳይ ውሳኔውን በጽኑ መደገፏን አስታውሰው፤ አሁንም ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲኾን ለማገዝ ዝግጁ እንደኾነች አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አይነተኛ ሚና እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአፍሪካ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
125 ዓመታትን ያስቆጠረውን የኢትዮ-ፈረንሳይ ወዳጅነት በመዘከር በቀጣይ በበርካታ ጉዳዮች በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
ሁለቱ ሀገሮች በታዳሽ ኃይል በተለይም ደግሞ ጂኦተርማል፣ ሎጂስቲክስና በግብርናው መስክ በጋራ እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል፡፡
የፈረንሳይ ባለሙያዎች ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ተቋርጦ የነበረውን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ዳግም ማስጀመር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር በሚከናወነው ሥራ ላይ ፈረንሳይ ተሳታፊ መኾኗንም ጠቅሰዋል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/