የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ዛሬ ተጀምሯል። 

167

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2012 ዓ/ም (አብመድ) የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና በጎንደር ከተማ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ መደበኛ የጥገና በጀት ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ እንደተናሩት ጥገናው የሚሠራው ከተማ አስተዳድሩ በየዓመቱ ለጥገና በሚመድበው መደበኛ የጥገና በጀት ነው።

 

ዛሬ ጥገናው የተጀመረው 12ኛው በር (ተዝካር በር) ነው። በ2011 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ይህ በር 12ኛ በር በመሆን ያገለግል የነበረ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም የጤና ተቋም ተሰርቶበት ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ ማተሚያ ቤት በመሆን ያገለግል እንደነበር የመምሪያው የቅርስ ጥገና ባለሙያ ዳዊት ተስፋ አመልክተዋል።

በጥናት በመመሥረትም ነባሩን አጥር የማስከበርና የማጠር ሥራ ተጀምሯል። የዕድሳት ግንባታው ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም በበጀት እና በግብዓት እጥረት ምክንያት ሲቋረጥ ቆይቷል።

 

ለግንባታ ጥቅም ላይ የሚውለው ግብዓት ባሕሪ ረዘም ያለ ጊዜ ጥናት ስለሚፈልግ በጥንቃቄ እንደሚሠራ ነው የጎንደር ከተማ አስተዳድር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥገና ባለሙያ ዳዊት ተስፋ ያመለከቱት።

 

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ደግሞ በተያዘው ዓመት የአጥር እና የመዋኛ ገንዳ ጥገናው በመደበኛ በጀት አንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል። በተለይም ዛሬ ግንባታው የተጀመረውን የአጥር ግንባታ በማጠናቀቅ በግቢው ያለውን አላስፈላጊ ቁሳቁስ የማስወገድ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናዎናቸውንም ገልጸዋል።

 

እንደ ኃላፊው ገለጻ ከተማ አስተዳድሩ ለሠራተኞች ክፍያ 2 ሚሊዮን ብር መድቧል። ለእድሳት ግብዓት የሚያገለግል ኖራም ተዘጋጅቷል።

 

የቅርስ ጥገና ባለሙያው እንደተናገሩት የእድሳት ሥራው ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የሚከናወን ነው። ግንባታው የሚከናወነውም የኖራ ግብዓትን በመጠቀም ነው።

 

በቅድሚያ በካልሼም ካርቦኔት የበለጸገ ኖራ በማቃጠል እና በመፍጨት የካልሼም ይዘቱን ወደ ካልሺዬም ኦክሳይድ እንዲቀየር ይደረጋል። ከዚያም የተፈጨውን ኖራ ከውኃ ጋር ቀላቅሎ ለረጅም ጊዜ በመቅበር ውሕዱ ወደ ካልሺዬም ሀይድሮ ኦክሳይድ እንዲቀየር ይደረጋል። በመጨረሻም ካልሺዬም ሀይድሮ ኦክሳይዱ ለግንባታ እንዲውል ይደረጋል ተብሏል።

 

‹‹ካልሺዬም ሀይድሮ ኦክሳይዱ ግንባታ ከተሠራበት በኋላ ይዘቱ ተመልሶ ወደ ካልሺዬም ካርቦኔት ይቀየርና ከፍተኛ ጥንካሬ እንዲኖረው ያደርገዋል›› ብለውናል የቅርስ ጥገና ባለሙያው፡፡

 

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleየሃገር ውስጥ ስፖርት ዜና
Next articleአልማ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ በክልሉ ሰብዓዊ ልማት ላይ አተኩሮ ሊሠራ ነው፡፡