
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ በውይይቱ የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) መልስ ሰጥተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ስለኾነ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል ነው ያሉት፡፡ በተለይም የንግድ ሥርዐቱና የገበያ እና የሸቀጥ ሥርጭቱ አግባብ ባለው መንገድ እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት በሕግና በሥርዐት በመቆጣጠር መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ የግብርና ግብዓቶችን አቅርቦት በተመለከተ ከክልሉ አስፈፃሚ አካላት ጋር ቀድመን ተወያይተንበታል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተለይም የአፈር ማዳበሪያ በውጫዊ ችግር ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለመሻገር ከአርሶአደሮች ጋር በመመካከር አማራጮችን እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡
የምርጥ ዘር አቅርቦትን እጥረትን ለመቅረፍም የተለየ ስልት ነድፈን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የግብርና ቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ለማዘመንና የመስኖ ሥራን ለማሻሻል በዚህ ዓመት ከበጀት በተጨማሪ 170 ሚሊዮን ብር መድበን እየሠራን ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ትልልቅ መስኖ ግድቦቻችን የግንባታ ሂደት የዘገየ ቢኾንም በጥረታችን ወደሥራ ገብተው አርሶአደሩን እንዲጠቅሙ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በፌደራሉ መንግሥት ባለቤትነት ተይዘው በክልሉ የሚከናወኑ የመንገድ፣ የመብራት፣ የድልድይ፣ የውኃና የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ልማት ወሳኝነት ስላላቸው ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዋግኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ በከፊልና ሌሎች አካባቢዎች ከመወረር መልስ እስካሁን ገና መብራት ያላገኙ አካባቢዎች ናቸው ያሉት ዶክተር ይልቃል በአማራ ክልል እንዲገነቡ ከተያዙ 22 የመብራት ኃይል ማሰራጫ ጣቢያዎች ውስጥ ገና 6ቱ ብቻ ግንባታቸው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የተጀመሩት ፈጥነው እንዲጠናቀቁና ያልተጀመሩትም ግንባታቸው እንዲጀመር ከፌደራል መንግሥት ጋር ኾነን በመሥራት የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦትን ለማዳረስና የኀይል መቆራረጥን ለማስቀረት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አመራርና ባለሙያዎች ቅን ኾነው ማገልገል አለባቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም እንዲሻሻል በስምሪት እንሠራለን ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ድህነት የተንሰራፋበት ክልል ስለሆነ ይህንን ለመቅረፍ ሰፊ ትግል ማድረግ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/