
መጋቢት 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል እና በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የመንግሥት ሃብት አሥተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሲሪንቃ ግብርና ምርምር ሐይቅ ንዑስ ማዕከል የተጠለሉ ወገኖችን ጎብኝተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ 34 ሺህ ተፈናቃዮች መካከል 29 ሺህ የሚኾኑት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ።
በመጠለያ ጣቢያው የተሟላ ቀለብ እንደማይቀርብላቸውና የሚቀርበውም በቂ ባለመኾኑ መቸገራቸውን የገለጹት ተፈናቃዮቹ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ብቻ ሳይኾን በዞንና ወረዳ ባሉ አንዳንድ የመንግሥት አመራሮች የታገዘ መፈናቀል የደረሰባቸው መኾኑንም ጠቅሰዋል።
“በመሥራት ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የምንተርፍ ነበርን” ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ ተቸግረን የሌሎችን እጅ ጠባቂ በመኾናችን የሞራልም ጉዳት ደርሶብናል ብለዋል።
አሁንም ቢኾን በወለጋ አካባቢ በርካታ ወገኖች መንገድ ተዘግቶባቸው በከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ላይ የሚገኙ በመኾናቸው መንግሥት ሊደርስላቸው ይገባል ነው ያሉት።
በዜጎች ሞትና መፈናቀል ዙሪያ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች በተጨማሪ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ የአመራር አካላት እጅ ሊኖርበት ይችላል ያሉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል፤ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ጥቃቶች በኹሉም አቅጣጫዎች በአንድ ጊዜ ተከፍተው አስቸጋሪ ቢመስሉም በዚህ አይቀጥሉም፤ ችግሮችን በጊዜ ሂደት እንፈታቸዋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
የብሔር ነጋዴዎች የሚያደርሱት ሰቆቃና በደል የወጡበትን ማኅበረሰብ ጭምር የሚያጠቃ መኾኑን ገልጸዋል።
ኾኖም ችግሩ በዚህ አይቀጥልም፤ መንግሥትም የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የመንግሥት ሃብት አሥተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባር መጠኑ የሚለያይ ቢኾንም ለየትኛውም ማኅበረሰብ የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አለመኾኑን ተናግረዋል።
በመኾኑም በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ወገኖች እንዳይፈናቀሉ፣ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱና ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ሠርተው እንዲኖሩ ማድረግ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት ኾኖ ይቀጥላል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ንጹሐንን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉና ሀብታቸውን እያወደሙ ያሉ የግጭት ነጋዴዎች በዚህ አይቀጥሉም ያሉት ዶክተር ግርማ፤ የክልሉ መንግሥት የዚህን ወንጀል ተዋናዮች ለማጥፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በኹሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ በማከናወን ላይ መኾኑንም ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/