የአሸባሪውን የትግራይ ቡድን የዳግም ወረራ ዝግጅት ለመቀልበስ ጠንካራ የውስጥ ዝግጅት ማድረግ እና አንድነትን መጠበቅ እንደሚገባ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

240

ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው የሥራ አፈፃፀም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ያቀረቡት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ደንብ በማውጣት የኅልውና ዘመቻው እንዲያሳካ አድርጓል ብለዋል። በክልሉ ከተወሰኑ የልማት ተቋማት ውጭ በጀቱና የሰው ኃይሉ ወረራውን ለመቀልበስ መዞሩንም አስታውሰዋል። ከፌዴራል መንግሥት ጋር የተቀናጀ ክልላዊ ኮማንድ ፖስትና ክልላዊ የዘመቻ አስተባባሪ በማቋቋም ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
በአንድነት መንፈስ የተከናወነው የኅልውና ዘመቻ ወራሪውን ቡድን ለመቀልበስ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱንም ተናግረዋል። ወደፊትም የጋራ ጉዳዮችን ተቀናጅቶ መሥራት ተጠናክሮ መቀጠል አለብትም ነው ያሉት። የፀጥታ መዋቅሩን ለማጠናከርና የአማራ ክልልን የመከላከያ ሠራዊት ተዋጽኦ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱንም አስታውቀዋል።
ለመከላከያ ግንባታ ሂደት ክልሉ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት። በክልሉ መከላከያ ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም አስታውቀዋል። ወጣቶች አሁንም መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ በማድረግ የምክር ቤት አባላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በኅልውና ዘመቻው የሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ሥራ በትኩረት እንደተሠራበትም አስታውቀዋል።
ዜጎች ለኅልውና ዘመቻው ድጋፍ እንዲያደርጉ መደረጉንም ገልጸዋል። የኅልውና ዘመቻው ሁሉም አካል ባለቤት ሆኖ የሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በኅልውና ዘመቻው የሕይወት መስዋእትነት ጭምር ዋጋ ለከፈሉ ኹሉ ምሥጋና አቅርበዋል። በወራሪው ኃይል የደረሰውን ጉዳት ማጥናት፣ ተፈናቃዮችን መመለስ መልሶ የማቋቋም ግንባታ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ወራሪው ቡድን በአማራ ክልል ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም አስታውቋል። ሕዝብን ጭካኔ በተመላበት መንገድ ጨፍጭፏል፣ ሃብትና ንብረት ዘርፏል ነው ያሉት። ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ ተፈናቅሎ በስቃይ ውስጥ መሆኑንም ገልፀዋል። በተደረገው መልሶ የማቋቋም ሥራ ከ1 ሚሊዮን 143 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ጠቁመዋል። ሳይፈናቀሉ በጦርነቱ ምክንያት ችግር ለገጠማቸው 9 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉንም አስታውቀዋል።
አሁን በሌሎች ክልሎች እና የሽብር ቡድኑ በያዛቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አመላክተዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የትብብር መንፈስ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በምሥራቅ አማራ የተጎዱትን የማቋቋም፣ የተቋረጡት ፕሮጀክት መልሶ የማስጀመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብና መላው ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ቡድን ለመደምሰስ ባደረጉት ርብርብ አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል። ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው የሽብር ቡድኑ አሁንም ለድጋሜ ወረራ ራሱን እያዘጋጀ ነው ብለዋል። በወራሪው ቡድን የታያዙ የክልላችን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ማስለቀቅ ይኖርብናል ነው ያሉት። ፅንፈኛው ቡድን እስከመጨረሻው ለሀገርና ለሕዝብ ስጋት በማይሆንበት ሁኔታ ለማድረስ መደራጀት እና የውስጥ አንድነታችን ማጠናከር አለብን ብለዋል ርእሰ መሥተዳደሩ።
እስካሁን በተደረገው ትግል የተገኘውን ድል መጠበቅ፣ የበለጠ ማጠናከር፣ አማራን ለማዋረድ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ አስተባባሪዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የአሸባሪውን ቡድን የዳግም ወረራ ዝግጅት ታሳቢ ያደረገ የውስጥ ዝግጅት እና አንድነት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ወራሪውን ቡድን መመከት፣ አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለውን ሴራ ማምከን፣ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ትኩረት መሆኑንም አስታውቀዋል። በሕልውና ዘመቻው የታየው አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሠራም ገልፀዋል።
ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት የክልሉ መንግሥት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የጀመረውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅና ከጥቃት መከላከል የሚያስችል የኀይል ግንባታ ተግባር በአግባቡ ታቅዶ በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ያነሷቸው ጥያቄዎችና ሐሳቦች: