በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የኹሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተገለጸ፡፡

137

መጋቢት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚጥልም ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍ ይሻሉ፡፡ በርካቶችም ከቤትና ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣብያ ውስጥ እያሳላፉ ነው፡፡ አሸባሪው የትግራይ ቡድን በአማራ ክልል ባደረገው ወረራ ዜጎችን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ የዕለት ጉርስ እንዲያጡም አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ እያሱ መስፍን በአሸባሪው ቡድን ምክንያት በርካታ ዜጎች ለከፋ ችግርና ሞት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠላት የዋግኽምራ ብሔረሰብን ሙሉ ለሙሉ ባለመልቀቁ በጠላት በተያዙ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለከፋ ችግርና ለመድኃኒት እጦት መጋለጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ በርካታ ዜጎችም አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን ግፍና መከራ ለቅቀው የሚወጡ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ በተጠናከረ ሁኔታ ቢቀጥልም አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በመደገጋፍ እሴት ችግሩን ለመሻገር እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑ በያዛቸው አካባቢዎች ገብተው ሕዝብ መታደግ አለመቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኀላፊው እንደገለጹት የዕለት ደራሽ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የመልሶ ማቋቋም ሥራም ይሠራል፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው ይሠራላቸዋል፣ ጥገና የሚያስፈልገው ይጠገንለታልም ብለዋል፡፡

መልሶ የማቋቋሙ ሥራ የክልሉ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት እንደሚኾንም አስታውቀዋል፡፡ ዜጎች አምርተው ራሳቸውን እንዲችሉና ችግሩን እስኪሻገሩ ድረስ ድጋፉ እንደሚቀጥል ነው የተገለጸው፡፡

የተፈጠረው ችግር የአማራ ክልልን ለማተራመስና ችግር ውስጥ ለመጣል በእብሪት በወረረው የትግራይ ወራሪ ቡድን መኾኑን አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ፋታ እንዳያገኝ፣ በከፋ ችግር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ይህን አውቆ በመረዳዳት እና በመደጋጋፍ ባሕሉ ለኅልውና ዘመቻው እንዳደረገው ኹሉ በደራሽ ድጋፉና በመልሶ ማቋቋሙም ሥራ እንዲያግዝም ነው የጠየቁት፡፡

ሕዝቡ ከችግር ወጥቶ፣ የአሁኑን ችግር ታሪክ አድርጎ ራሱን የሚያቋቁምበትን አሠራር መፍጠር አለብንም ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ትናንት ያሳየውን መደጋጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃትና በወራሪው ቡድን ወረራ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በወረረው አካባቢ ተመትቶ ሲለቅም በወረራው ወቅት ባደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ሕዝቡ በረሃብና በመድኃኒት እጦት መጎዳቱንም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል፡፡ ድጋፍ የሚሹትን ዜጎች ለመደገፍም የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መኾኑን ነው ያስታወቁት፡፡

የክልሉና የፌደራል መንግሥት ባቀረቡት ጥሪ መሠረት ረጅ ድርጅቶች በበርካታ አካባቢዎች ገብተው ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የፌደራል መንግሥትም ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በፌደራል መንግሥት የሚቀርበው የምግብ አቅርቦት የመዘግየትና የመቆራረጥ ችግር እንዳለም አስታውቀዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለመደገፍ በወር ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ኩንታል እህል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ታላቅ አቅም የሚጠይቀውን አቅርቦት መንግሥት ብቻውን ሊቋቋመው ስለማይችል መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች አካላት ከመንግሥት ጎን በመቆም ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

እስካሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ እየቀረበ ያለው በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት፣ በባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍል መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

ለተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሌሎች ድጋፎች መደረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

በአመልድ ኢትዮጵያ የግብርና ሥርዐተ ምግብና አደጋ መከላከል ሥራ አመራር ዳይሬክተር ግርማ ዘውዴ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁለት ፕሮግራሞች የምግብ እህል ድጋፍ የማድረግ ሥራ እያከናወኑ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቋሚ ለኾኑና ቋሚ ላልኾኑ ተረጂዎች ከጻግብጂ ውጭ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

የጻግብጂ ወረዳ በጠላት እጅ የተያዘ በመኾኑ ለዜጎች ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ወደ ሰቆጣ እየመጡ ድጋፍ እንዲወስዱ የማመቻቸት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጆፕ በሚል ፕሮግራም በአራተኛ ዙር ከ332 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የምግብ እህል ማሰራጨታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአምስተኛ ዙር ደግሞ ከ439 ሺህ በላይ ዘጎች የምግብ እህል ማሰራጨት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ ፕሮግራሞቻቸው በቋሚነት ችግር ውስጥ ያሉና በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የሚቸገሩ ዜጎችን የሚደግፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው መጨመር ለሥራው ችግር መኾኑንም አንስተዋል፡፡

በመደበኛ ድጋፍ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ግን ትርጉም ያለው ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአራት ወረዳዎች በመደበኛነት የስድስት ወር ድጋፍ የሚደረግላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡ በቋሚነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የብልጽግና ፖርቲ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በጨለማ ውስጥ እየኖረ ላለው ሕዝብ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል” የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“ኤች. አር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎች የኢትዮጵያ እና አሜሪካ የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት የማያንፀባርቁ ናቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን