
ሑመራ: መጋቢት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፖርቲ ያካሄደውን ጉባኤ መነሻ በማድረግ በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በሑመራ ከተማ ከማሕበረሰቡ ጋር መክሯል።
የክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ያላለም ፈንታሁን፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም አያሌው፣ የዞን አመራሮች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም የከተማዋ ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት በማንነታቸው ምክንያት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተለያየ ግፍና ጭቆና ሲደርስባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ገዥው ፓርቲ በዞኑ ከአንድ ዓመት በላይ የተቋረጠውን የመብራት አገልግሎት ችግር አለመቅረፉ እና የተለያዩ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ አለመገንባቱን እንደ ትልቅ ክፍተት የጠቀሱት ነዋሪዎቹ የዞኑ ሕዝብ ነፃነቱን ቢጎናፀፍም አሁንም በጨለማ ውስጥ ነውና ፓርቲው ለዞኑ በጀት በመመደብ ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ ያሉትን ችግሮች እንዲቀርፍላቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
በመድረኩ መፈጠር ደስተኛ መኾናቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ በዞኑ የፍትሕ ተቋማት ባለ መዋቀራቸው እየተንገላታን ነው፤ መንግሥት ወደ ሥራ ያልገቡ መዋቅሮቹን በመዘርጋት የፍትሕ ተጠቃሚ ሊያደርገን ይገባል ብለዋል።
ፓርቲው የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አስተማማኝ ለማድረግ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሥር የሚገኙ ቦታዎች ነፃ እንዲሆኑ አቅጣጫ አስቀምጦ ከሕብረተሰቡ ጋር ሊሥራ እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቅሰዋል።
ከሕብረተሰቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ጎሹ ውይይቱ የተፈጠረው የሕዝቡን ጥያቄ ለማድመጥና ለቀጣይ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማስቀመጥ በመኾኑ የሕብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ፓርቲያችን ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት አማራ በመኾናቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ዞኑ ከከተማና ከወረዳ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል ያሉት ኃላፊው በዞኑ ሕገወጥነትን ለማስቆም ኮሚቴ ተዋቅሮ በሥራ ላይ መኾኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች ለፓርቲው ጠቃሚ በመኾናቸው በእቅድ ተይዘው የምንሠራባቸው ይኾናሉ ነው ያሉት።
“ማንነታችንና ወንድማማችነታችን የማይነጣጠል በመኾኑ ከጎጃም እስከ ሑመራ በነፃነታችን መፍለቂያ ምድር የተገኘነው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የእኛም በመኾኑ ነው” ያሉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪና የብልጽግና ፖርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም አያሌ ናቸው።
አቶ አብርሃም ያጋጠሙንን እንቅፋቶች ለመሻገር አንድነታችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመኾን የሀገር ውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊያስከብር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጥያቄ በደም የተገኘ በመኾኑ ማንም የማይነጥቀን ማንነታችን ነው፤ አካባቢያችንን ለማልማት ጠንክረን ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ያላለም ፈንታሁን በእናንተ ጫማ ተራምደን ችግራችሁን ተካፍለን መፍትሔ ለማምጣትና ሰላማችንን ለማስጠበቅ ከእናንተ ጋር እንሠራለን ብለዋል።
ፓርቲያችን ከፈተና ወደ ልዕልና ከፍ እያለ የመጣ በመኾኑ ይህ ከፍታ ያለ እናንተ ዋጋ ስለማይኖረው የተነሱ የመብራት፣ የውኃ፣ የባንክ እና የትምህርት ቤቶች መዘጋትን ለመቅረፍ እናንተን ወክለን የወልቃይትን ጥያቄ እናስፈፅማለን ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት በጦርነት ውስጥ ኾኖ እያደረገ ላለው ድጋፍም ነዋሪዎቹ አመስግነዋል።
ዘጋቢ:–ያየህ ፈንቴ ከሑመራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/