“ጦርነቱ እና የጸጥታ መደፍረሱ በተፈታኝ ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የሚታወቅ ኾኖ ሳለ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩ በአግባቡ ሳይታይና ሳይፈተሸ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አወሳሰን ላይ የሚታይ ነገር የለም ማለቱ ተገቢ ውሳኔ አይደለም” የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

169

መጋቢት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የ2013 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን አስመልከቶ በቀረበ ቅሬታና የተካሄደ ምርመራን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን አስመልክቶ ለተቋሙ የቀረቡ ጥቆማዎች እና በተለያዩ ሚዲያዎች ጉዳዩን አስመልክቶ የቀረቡ ዘገባዎችን መነሻ በማድረግ ችግሮችን በምርመራ በመለየት ተገቢውን የመፍትሔ ሐሳብ ለመስጠት በተደረገ የራስ ተነሳሽነት ምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሁለተኛ ዙር ፈተና እርማት ላይ ስህተቶች የተፈጠሩ መሆኑን የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ በምርመራ ሂደት ወቅት ለተቋሙ መርማሪዎች አረጋግጧል፡፡
በተጨባጭም የእርማት ስሕተት አለ በሚል ቅሬታ ካቀረቡ ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ድጋሚ እርማት በተደረገ ወቅት ስሕተት የተፈጠረ መኾኑን ማሳያ ወይም ማረጋገጫ መኾን የሚችሉ የማስተካካያ እርማቶች እና ውጤቶች መከሰታቸው በእርማት ሂደቱ ላይ ችግሮች መፈጠራቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መኾናቸውን ተቋሙ አረጋግጧል ብሏል፡፡
የቀረቡ አቤቱታዎችን መሠረት አድርጎ በተካሄደ ምርመራና ግኝትም የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ተማሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል ምላሽ መስጠቱን የገለጸ ቢኾንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መርመሪዎች ለምርመራ ሥራ በኤጀንሲው በተገኙበት ወቅት በርካታ ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ በኤጀንሲው ቢገኙም ወደ ውስጥ ገብቶ ቅሬታን ለማቅረብም ሆነ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ ይልቁንም ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል ብሏል መግለጫው፡፡
ቅሬታቸውን ይዘው ወደ በትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የፈተናዎች ኤጀንሲ ነው በሚል ቅሬታቸውን ሳይቀበል የቀረ መኾኑን እና በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ መጥተው ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙ የተቋሙ መርማሪዎች በቦታው በመገኘት እንዳረጋገጠ ገልጿል፡፡
ማንኛውም ዜጋ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ ለሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ተቋም የማቅረብ መብት እንዳለውና ቅሬታ የቀረበለት አካልም ቅሬታውን ተቀብሎ ያለምንም ገደብ ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 20፣21፣22፣23 እና ተከታዮቹ መሰረት ግዴታ ያለበት መሆኑን በአዋጁ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የፈተናዎች ኤጀንሲ እና ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ የተጣለባቸውን ኀላፊነት ከመወጣት ይልቅ ቅሬታዎችን አጣርተን ጨርሰናል እና ጉዳዩ እኛን አይመለከትም በሚሉ ተገቢ ባልኾኑ ምክንያቶች የተማሪዎችን ቅሬታ ለመቀበል ፍቃደኛ አለመኾናቸው ከአዋጅ ቁጥር 1183/2012 አኳያ አሥተዳደራዊ በደል መኾኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አረጋግጧል ነው ያለው፡፡
“ጦርነቱ እና የጸጥታ መደፍረሱ በተፈታኝ ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የሚታወቅ ኾኖ ሳለ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩ በአግባቡ ሳይታይና ሳይፈተሸ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አወሳሰን ላይ የሚታይ ነገር የለም ማለቱ ከመልካም አሥተዳደር መርሆች አኳያ ተገቢ የኾነ ውሳኔ አይደለም” ብሏል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፡፡
በተቋሙ የተሰጠ የመፍትሔ ሐሳብ
1. ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተገቢውን ጊዜ ሰጥቶ ያለምንም ገደብ በአካል፣ ኦንላይን (online) የአቤቱታ ማቅረቢያ ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ አቤቱታዎች በመቀበል ተገቢውን የሰው ሀይል በመመደብ ለቅሬታዎቹ ግልጽ እና ምክንያታዊ ምላሽ እንዲሰጥ፡፡ በተለይ በኦንላይን(online) ለቀረቡ አቤቱታዎች እየተሰጡ ያሉ ምላሾች በአግባቡ የታዩ እና ማጣራት የተደረገባቸው ስለመሆናቸው ተገቢው ቁጥጥር እንዲደረግባቸው፤
2. በ2013 ዓ/ም የትምህርት ዘመን በሁለተኛ ዙር የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የፈተና እርማት ሂደት ላይ ስህተቶች የተፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል ስለዚህ በሁለተኛው ዙር እርማት ተጨማሪ ስህተት አለመኖሩን ድርጅቱ በሚያረጋግጥበት ስርአት (verification) አረጋግጦ ለአቤት ባዮች አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፤
3. የትምህርት ሚኒስቴር በጦርነት ወይም የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አከባቢዎች የተመዘገበውን የተማሪዎች ዉጤት በአንጻራዊነት ሰላም በነበረባቸው አካባቢዎች ከተፈኑ ተማሪዎች ዉጤት ጋር ያለውን ልዩነት (Variation) ወይም ተቀራራቢነት በማየት እና በሚያገኘው ግኝት መሰረት የተማሪዎች ወደ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስገባው መቁረጫ ዉጤት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ዳግም ማየት የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር ምክንያቱም ተቋማት የሚሰጡት ምላሽ በተማሪዎች ህመም ውስጥ ሆነው መሆን ስላለበት፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“መንግሥት ሰላምና ደኅንነታችን ሊያስከብርልን ይገባል” የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች
Next article“የብልጽግና ፖርቲ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በጨለማ ውስጥ እየኖረ ላለው ሕዝብ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል” የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች