“ኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ኹሉም ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ ይገባል” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

265

መጋቢት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ በመጣል ተፅዕኖ ለማድረግ በአሜሪካን ኮንግረንስ አባላት እየተቀነቀነ የሚገኘውን ኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲረባረቡ ተጠየቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደገለጹት፤ ኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ ይዘት ኢትዮጵያን ኹለንተናዊ በኾነ መልኩ የሚጎዳ ነው። ስለዚህም ሕጉ እንዳይጸድቅ ኹሉም ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ኾነው ይህን ረቂቅ ለማስቆም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አሜሪካኖችም ጭምር ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ ሕጉን የሚደግፉ የኮንግረሱን አባላት በማነጋገር እና ተቃውሞዎችን በማሰማት ይህ ሕግ እንዳይጸድቅ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን እና የወዳጅ ሀገራት መንግሥታትን በማነጋገር በአጠቃላይ በአሜሪካ መንግሥት ላይና በኮንግረንሱ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት ጦርነት መኾኑ እየታወቀ በአሜሪካ በኩል የአሸባሪን ወገን ደግፎ እንደዚህ ዓይነት ረቂቆችን ማስኬድ ስሕተት ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ የረቂቅ ሕጉ መጽደቅ ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፍ መኾኑንም ተናግረዋል።
ኤች.አር 6600 ረቂቅ መፅደቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላም ለማውረድ የሚረዳ ብሔራዊ ምክክር ለመፍጠር መንግሥት እያደረገ ያለውንም ጥረት የሚያደናቅፍ እና የኹለቱን ሀገራት የቆዬ ግንኙነት የሚጎዳ ነው። ከዚህም አልፎ የአካባቢውንም ሰላምና ደኅንነት ችግር ውስጥ የሚጥል እንደኾነም ጠቁመዋል።
ኤች.አር 6600 ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ ማዕቀብ ስለሚኾንና አሁን የተጀመረውን የሰላም ጥረት ስለሚያደናቅፍ በተለይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለመደ አንድነታቸው እንዲቀለብሱት ጥሪ አቅርበዋል።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠና በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ትክክል ያልኾነና አግባብነት የሌለው መኾኑንም አምባሳደሩ አመላክተዋል።
ኤች.አር 6600 የኹለቱን ሀገራት ግንኙነት ቁመና የማይመጥንና አግባብነት የሌለው ረቂቅ ሕግ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የመንግሥት አካላት ከሚሠሩት ሥራ በተጨማሪ የሕዝቡ ጫና የመፍጠር አቅም ከፍተኛ ስለኾነ ይህን አቅም መጠቀም ይገባል ብለዋል።
መንግሥት በኤምባሲዎቹ፣ በቆንስላ ጽሕፈት ቤቶቹና የዳያስፖራ ዳይሬክተር ጀነራሎቹ በኩል የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። አሁንም የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግን ለማስቆም ጥረቶች በመደረግ ላይ መኾኑን መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣ ምንስ ኾኜ ምን ላርጋቸው”
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቻይና ኢስተርን አየር መንገድ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ፡፡