
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከአማራ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለክልል ምክር ቤት የተመረጡ አባላት በተመጡበት የምርጫ ክልል ሲያካሂዱ የቆዩት የመራጭ ተመራጭ መድረክ ማጠቃለያ መርኃግብር ተካሂዷል።
በመርኃግብሩ የክልሉ ዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮችን የወከሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ አባላት የወከሉትን ሕዝብ ዋና ዋና ያሉትን የሕዝብ ጥያቄዎችና ችግሮች አንስተዋል። በሕዝብ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመለየት ምላሽ መስጠት በሚያስችልበት ሁኔታ ላይ ነው የመከሩት።
የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጮች አስተባባሪና በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በክልሉ ከዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮች ሕዝብ የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሕዝቡ በድጋሚ ወረራ ሊፈጸም ይችላል የሚል የጸጥታ ስጋት ከሕዝቡ በጥያቄ እንደሚነሳ ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነትና የግብርና ግብዓት እጥረት መኖር፣ በኅልውናው ዘመቻ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች መኾናቸውን አቶ ደሳለኝ አንስተዋል። የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በልዩ ሁኔታ መፈተን እንደነበረባቸው፣ ስርቆትና ሕገ ወጥነት ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች መኾናቸውን አስተባባሪው ጠቅሰዋል። የንጹሕ የመጠጥ ውኃ ችግር፣ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተጎዱ ዜጎች የካሳ ጥያቄ ስለማንሳታቸው፣ ከተሞች በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን ብቻ መቻል እንዳለባቸው አባላቱ አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ከአማራ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ የክልል ምክር ቤት ተወካዮች ለተነሱት ዋና ዋና ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ከሕዝብ የተነሱትን ጥያቄዎች ክልሉ በግብዓትነት ወስዶ የሚሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የሰላምና የደኅንነት ችግሮች አስመልክቶ የተነሱ ጉዳዮች ትክክል መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የራሱ የኾነ ግዙፍ የጸጥታ ኀይል እየገነባ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። ልዩ ኀይሉ ተጠናክሮ የሕዝቡ መከታ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑ ነው የገለጹት። ሕዝብን ሳያገለግሉ የቀሩ የፖሊስ የሥራ ኀላፊዎች ከኀላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንም አንስተዋል።
ፋኖ በኅልውና ዘመቻው ላይ የከፈለው መስዋእትነት ከፍተኛ በመኾኑ ሊመሰገን ይገባዋል ያሉት ዶክተር ይልቃል ከጦርነቱ በኋላ ግን “ፋኖ ነኝ” እያሉ በፋኖ ስም ችግር የሚፈጥሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።
ፋኖ የታሪካችንና የባሕላችን መገለጫ እንጂ የራሱን ሕዝብ የሚገድልና የሚዘርፍ አይደለም ብለዋል።
ለሕግ ተገዢ የኾኑ ከመንግሥት ጎን የሚሰለፉና በምሽግ የሚገኙ ፋኖዎች በመኖራቸው መከበር አለባቸው ነው ያሉት።
ርእሰ መሥተዳደሩ እንዳሉት በክልሉ የሚታዩ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች መልክ መያዝ አለባቸው። በየደረጃው የሚገኙት የሥራ ኀላፊዎች የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቅ ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመኾን የመንገድ ግንባታ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የኤሌክትሪክ ኀይል ችግር ለመቅረፍ በክልሉ 22 ሰብስቴሽኖች እንዲኖር ለማድረግ መታቀዱንም ተናግረዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየተሠራ ነውም ብለዋል። የኑሮ ውድነቱ ውጫዊ ጫናም ስላለበት የጋራ መግባባት መፍጠር አለብን ነው ያሉት።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ 41 ሺህ ሄክታር መሬት በቆላ ስንዴ መሸፈኑ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል። በዚኽም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በመኖሩ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅ መደረጉን ጠቁመዋል።
“የአማራ ክልል መንግሥት ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ቀጥሎ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል” ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 18 በመቶ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ መደረጉ አግባብነት ስለሌለው ችግሩ መጣራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ሠራተኛውም ኾነ አመራሩ በአግባቡ ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በየከተሞቹ የአመራር ግምገማ መደረጉንም አመላክተዋል።
የክልሉ ከተሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲለሙና እንዲያድጉ እንሠራለን ብለዋል። በቀጣይ ኹሉም ከተሞች ከሚያመነጩት ሀብት ለሌላው ማካፈል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖች ተመልሰው እንዲቋቋሙ ከኹሉም ክልሎች የተዋቀረ ግብረኀይል መኖሩን ገልጸዋል። ከሁለቱም ክልሎች ጋር በጋራ መልማት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ መኾኑንም ርእሰ መሥተዳደሩ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙትም የመልማት፣ የሰላምና የማደግ ተስፋ ስላለው ከምንግዜውም በላይ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/