
ሑመራ: መጋቢት 12/2014 ዓ.ም ክንዳቸው ነበልባል፣ አፈ ሙዛቸው የሚያቃጥል፣ ለወደዱት ፀዓዳ፣ ለጠሉት ፊታቸው እንደ ረመጥ የሚፋጅ፣ እንኳን ተኩሰው ወርውረው የማይስቱ፣ የደጋዎቹ መብረቅ፣ ቁጣቸው የጎመራ፣ በነፃነታቸው ለመጣ ከአፈር ሳይደባልቁ ዝንፍ የማይሉት የጠገዴ ወረዳ ሚሊሻዎች አሸባሪውን የትግራይ ቡድን ለመደምሰስ ዛሬም በግንባር ላይ ናቸው።
አልጠግብ ባይ ሆዳቸው፣ የስልጣን ጥማቸው ኅሊና የነሳቸው የአሸባሪው ቡድን አባላት ከአራት ኪሎ ወጥተው መቀሌ ላይ መሽገው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢጥሩም የማህፀነ ለምለሟ ልጆች የብረት አጥር በመኾን ወራሪውን ቡድን በመደምሰስ አንደኛውን የኅልውና ዘመቻ ምዕራፍ አጠናቀቅዋል።
በደም ያገኙትን ነፃነት አስጠብቆ ለመዝለቅና ወልቃይትን የአሸባሪው ቡድን መቀበሪያ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ ሚሊሻ አባላት ወራሪው ቡድን እስካልተደመሰሰ ድረስ እንቅልፍ አይወስደንም ሲሉ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል።
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ልጆቿን ሲገድል፣ ሲያሳድድ፣ ነጭ ወርቋን ሲቃርም፣ የተፈጥሮ ፀጋዋን ሲያግበሰብስ የነበረው የአሸባሪው ቡድን የወልቃይት ጠገዴን ምድር ለቆ ከወጣ በኋላ ዳግም በባርነት ለመያዝ የተለያየ ሙከራ ቢያደርግም በጀግናው የወገን ጦር ዶግ አመድ ኾኖ ሙትና ቁስለኛ ኾኗል።
በጠገዴ ወረዳ የሚሊሻ አባል የኾነው ቻላቸው ውበት “ለዓመታት በማንነታችን ብዙ መከራ ደርሶብናል፤ አሁን ያገኘነውን ነፃነት አስጠብቆ ለመዝለቅና አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በተጠንቀቅ ላይ ነን” ብሏል።
በኅልውና ዘመቻው ያስመዘገብነውን ድል አሁንም ሳንዘናጋ ዝናራችን ከወገባችን ሳይፈታ፣ አፈሙዛችን ከጠላት ላይ እንደተቀሰረ ነው።
ወራሪው ሳይደመሰስ ወደ ኋላ ላንመለስ ተማምለናል ያለን ሌላው የሚሊሻ አባል ምህረቱ አስማረ በንቃትና በተጠንቀቅ ላይ መኾናቸውንም ተናግሯል።
በወረዳው ሰርጎ ገብ እንዳይኖር በንቃት እየሠሩ እንደሚገኙ የወረዳው ትጥቅና ስንቅ ቡድን መሪ አስተባባሪ አለባው ሽባባው ገልጸዋል።
ወረዳው የስጋት ቀጣና መኾኑን የገለጹት አቶ አለባው አሁንም ድረስ የጠላት መግቢያ ቦታዎች ይኾናሉ ተብለው በታሰቡ ቁልፍ የግንባር ቦታዎች የሚሊሻ አባላቱ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በግንባር ላይ ለሚገኙ የሚሊሻ አባላቱም የስንቅ ድጋፍ በማድረግ ኅብረተሰቡ አሁንም ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
በወረዳው በኅልውና ዘመቻው በጀግንነት ተጋድሎ ለፈጸሙ የሚሊሻ አባላት ዕውቅና መሰጠቱን የገለፁት የጠገዴ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዋኘው ደሳለኝ ናቸው። በኅልውና ዘመቻው ለተሰው ጀግና የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ – ከጠገዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/