
መጋቢት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የወሰዱ የአማራ ክልል ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም የአማራ ክልል መንግሥትን እንዳስደነገጠው ነው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) የገለጹት፡፡
ዶክተር ማተብ ጉዳዩን አስመልክቶ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የክልሉ ተማሪዎች ውጤት ከሀገር አቀፍ አማካይ ውጤት አንጻር ዝቅተኛ መኾኑ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ውጤቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ያልተጠበቀ እና ግራ የሚያጋባ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ፈተና ተሰርቆ ወጥቷል በተባለ ጊዜ በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ቀደም ብሎ ለሀገር አቀፍ የትምሕርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ማሳወቁን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ይህንንም የመጀመሪያው ዙር ፈተና ባለቀ ማግስት ማሳወቃቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ ኾነው መፈተናቸው በውጤታቸው ላይ የተለዬ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥያቄ መቅረቡንም አንስተዋል፡፡ እንደ ክልል የትምሕርት ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች ለሕግ ማስከበር ዘምተዋል፤ መምህራን ሳይቀሩ ሀገር ሊያድኑ ግንባር ተሰልፈዋል፡፡ ይህም ለውጤቱ መቀነስ አንዱ ምክንያት እንደሚኾን ነው ያስታወቁት፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው አካሄድ የፈተና ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ክልሎች በተገኙበት ውይይት ይደረጋል፤ በዚሕ ዓመት ግን ውይይት አለመደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
ዶክተር ማተብ ‹‹ተሰርቆ የወጣው ፈተና በአግባቡ ሳይታይ ቀርቶ በክልሉ ተማሪዎች ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ ከኾነ፤ ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ መቆየታቸው በልዩ ኹኔታ ጎድቷቸው ከኾነ፤ በእርማት ሂደት የተፈጠሩ ስሕተቶች ካሉ እንዲታዩ ጥያቄ እያቀረብን ነው›› ብለዋል፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ጥያቄያቸውን ማቅረብ ያልቻሉ ተማሪዎች በዞኖች በኩል ጥያቄያቸውን አቅርበው ትምህርት ቢሮ ባለሙያ መድቦ እንዲያጣሩ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
“የተማሪዎች ውጤት መቀነስ እኛን ስለሚመለከት ችግሩ እስኪፈታ ቢሮው እስከመጨረሻ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
ትምህርትን የሚመራ አካል ከተማሪዎቹ የበለጠ ጉዳይ የለውም ያሉት ዶክተር ማተብ ከክልሉ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን በመርህና በሥርዐት ላይ የተመሠረተ አቋም ይዘን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/