“ርስት አልባ ባለ ርስቶች፣ ባለ ጸጋ ችግረኞች”

200

መጋቢት 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሚያጎርሱት ተርበዋል፣ የሚያጠጡት ተጠምተዋል፣ እንግዳ የሚያሳርፉት በመጠለያ ውስጥ በሐዘን ተቀምጠዋል፣ ለተቸገረ የሚደርሱት የሰው እጅ አይተው እንዲያድሩ ኾነዋል፡፡ ባለ ርስት ኾነው ሳለ ርስት አልባ ኾነዋል፣ ባለ ጸጋ ኾነው ሳለ ችግረኛ ኾነዋል፡፡ የግፍ ሥርዐት በባድማቸው ባዕዳ፣ በርስታቸው እንግዳ አድርጓቸዋል፡፡ ማንነታችን አትንኩ የእናነተንም አንነካም ባሉ መከራ በዝቶባቸዋል፡፡
በሚወዷት ቀያቸው፣ በሚያከብሯት ሀገራቸው በሰላምና በፍቅር እንዳይኖሩ በደለኞች እጃቸውን አንስተዋባቸዋል፡፡ በግፍ ገድለዋቸዋል፣ ከቀያቸው አሳድደዋቸዋል፣ እናትን ከልጇ እቅፍ ነጥለው ወስደዋል፣ አባትና ልጅ በአንድ ቤት ውስጥ እንዳይኖሩ ተደርገዋል፡፡ በዚያ ቀዬ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀ የእናት እንባ ፈስሷል፣ ለዓመታት የእናት አንጀት ተላውሷል፡፡ የምድሩ አፈር በንጹሐን ደም ርሷል፡፡
የራያ እናቶች ለዓመታት አንብተዋል፣ የራያ ጀግኖች ለማንነታቸው፣ ለሚወዷት ሀገራቸው ከመውዜራቸው ጋር ተማምለው፣ ዱር ቤቴ ብለው ለዓመታት ታግለዋል፣ አኹንም ትግል ላይ ናቸው፡፡
ጀግኖቹ በተመቸም ባልተመቸም ዘመን ውስጥ ኾነው ለማንነት ሲሉ ትግል ያደርጋሉ፣ የራያ ባላ፣ የራያ አላማጣና ሌሎች የራያ አካባቢዎች በሽብርተኛው ቡድን የግፍ ዶፍ እየወረደባቸው ነው፡፡ የሚወርድባቸውን የግፍ ዶፍ ለማምለጥ እኒያ ባለ ርስቶችና ባለ ጸጎች የነበሩ ዜጎች ባዶ እጃቸውን ልጆቻውን እያስከተሉ መሰደድ ግድ ኾኖባቸዋል፡፡

ከሞቀ ቤታቸው፣ ሀብትና ንብረት ካፈሩበት፣ ወልደው ከሳሙበት፣ አሽተው ከቃሙበት ቀያቸው ወጥተው በስደተኞች መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ነው፡፡
የራያ ባላ ነዋሪዎች ሰቆቃ ውስጥ ነን ነው የሚሉት፡፡ በራያ ባላ ውስጥ መውጣት ሳይችሉ ቀርተው በዚያው ያሉ ዜጎች እንጀራ ጋግረው መብላት እንዳይችሉ እየተደረጉ መኾናቸውን አካባቢያቸውን ለቅቀው የወጡት ነግረውናል፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት ጭስ በሚጨስበት፣ ወጥ በሚሠራበት፣ እንጀራ በሚጋገርበት ቤት እየዞሩ እየቀሙ ይበላሉ፡፡
እናት ለልጇ ልትሰጥ ያዘጋጀችው ምግብ ከእጅ ቀምተው ይበላሉ፣ ነዋሪዎቹ እህል እንዲያወጡ፣ ገንዘብ እንዲሰጡ፣ ወጣቶችና ሕጻናት ሳይቀር የሽብር ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ግዳጅ መጣሉንም ነግረውናል፡፡ በራያ ባላ ውስጥ የበሰለ እንጀራ መብላት አይቻልም፡፡ በማንነታቸው የሚሰቃዩት የራያ ባላ ወጣቶች ወገናቸውን እንዲወጉ እየተገደዱ፣ ወደ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲገቡ፣ እምቢ ያሉት ደግሞ ወደ ማይታወቅ ቦታ እየተወሰዱ፣ እየተገደሉም ነው ብለውናል፡፡ እኒህ ማንነታችን አትንኩን ያሉ ነዋሪዎች ብዙዎቹ ለወራት አካባቢያቸውን ጥለው እየተሰቃዩ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ በጠላት እጅ ውስጥ መከራው እየጸናባቸው ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ አባላት የእናቶችን መቀነት እየፈቱ፣ ኪስ እየፈተሹ እንደሚዘርፉ፣ በመሬታቸውም ከመሃል ትግራይ እያመጡ በይዞታ እየሰጧቸው መኾናቸውንም ነግረውናል፡፡ ባለ ርስቶቹ በቶሎ እንዲመለሱ ካልተደረገ መሬት አልባ፣ ለኹልጊዜም ተረጂዎች ኾነው እንደሚቀሩም ነግረውናል፡፡ የሽብር ቡድኑ ለዳግም ወረራ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንም አካባቢያቸውን ለቀው የወጡት ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የፈተና ጊዜ ውስጥ ነው ያሉን እናት እናታቸውን እና ልጃቸውን ጥለው መውጣታቸውን ነግረውናል፡፡ አኹን ላይ እናታቸው ታሥረው ልጃቸው መድረሻ እንዳጣ ነው የነገሩን፡፡ ለወራት በዘለቀው የመከራ ጊዜ ሴቶች በመጠለያ ውስጥ ወልደዋል፣ አኹንም ለመውለድ ቀናቸውን እየጠበቁ ያሉ አሉ፡፡ ወላጅ እናታቸው የወጡ ልጃቸውን ካላመጡ ተብለው እንደታሠሩም ነግረውናል፡፡
መንግሥት በአፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ቢኾንም በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ ወደ ቀያቸው መመለስ መኾኑንም ነው የነገሩን፡፡ ወጣቶቹ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንና ጠላትን ለመፋለም ዝግጁ መኾናቸውንም ነግረውናል፡፡ ወጣቶች ስልጠና ወስደው የሚሰጣቸውን ተልእኮ እንደሚጠባበቁም ነግረውናል፡፡
የራያ ባላ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሀብቱ ስዩም ወረዳው በጠላት እጅ ላይ ኾኖ ነዋሪዎቹ በደሎች እየደረሱባቸው ነው ብለዋል፡፡ የማኅበረሰቡ ስቃይ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የራያ ባላ ነዋሪዎች ሰቆቃውንና አፈናውን ለማምለጥ ቤታቸውን ጥለው ወደ ጫካ እየገቡ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ሌሊት ላይ እያፈነ ስለሚወስድ አካባቢውን ለቀው መውጣት ያልቻሉት በቤታቸው እንደማያድሩ ነው የተናሩት፡፡ ወጣቶች አካባቢውን ለቀው እየወጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የነዋሪዎቹን የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ እየነጠቁ እንደሚወስዱባቸው ተናግረዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ከመሃል ትግራይ ሰው እያመጣ በአካባቢው እያሰፈረ እና ለጦርነት እየተዘጋጀ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በራያ ባላ ነዋሪዎች ላይ እየጣለው ያለው ጠባሳ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
አካባቢያቸውን ለቅቀው የሚወጡ ዜጎችን በመቀበል ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ የማሳረፍ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በግፍ አካባቢያቸውን ለቅቀው ከሚወጡ ነዋሪዎች ጋር የሽብር ቡድኑ አባላት አብረው እንዳይገቡ ከፍተኛ የኾነ ጥንቃቄ እያደረጉ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በሥነ ልቦና ጠንካራ ኾኖና ሰልጥኖ ጠላቱን እንዲፋለም የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
መንግሥትም አካባቢው ነጻ ለማውጣት አቅጣጫ ያስቀምጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች በከፍተኛ ተነሳሽነትና ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙም ነግረውናል፡፡ በማንነቱ የኮራ ሕዝብ ተደራጅቶ ወደ አካባቢው በመግባት ጠላቱን ለማጥፋትና ነጻነቱን ለማዋጅ ከፍተኛ የኾነ ፍላጎትና ጥያቄ ያለው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከጠላት ጋር ተፋልመን አካባቢውን ነጻ እናወጣለን እንጂ በመጠለያ ጣብያ ውስጥ አንኖርም የሚለው ሰው ቁጥር በርካታ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
የራያ ሕዝብ በሥነልቦና ጠንካራ ኾኖ ጠላቱን እስከመጨረሻው ማስወገድ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
መንግሥትም እየተበደለ ላለው ሕዝብ በአስቸኳይ እንዲደርስለት ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየደሴ ዙሪያ ወረዳ አሥተዳደር አሸባሪውን የትግራይ ቡድን ለመደምሰስ በተካሄደው የኅልውና ዘመቻ በጀግንነት ተጋድሎ ለፈጸሙ የጸጥታ ኀይሎች እውቅና ሰጠ።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኦክስፋም በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አደነቁ።