የዋግ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲያርሱ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

195

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ እና ጻግብጅ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ፣ ዝቋላ እና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ደግሞ በከፊል በሽብር ቡድኑ በቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች 54 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሎ ለችግር ተዳርጓል። መንግሥት በወረራ የተያዙ አካባቢዎችን ነጻ በማውጣት ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመልሳቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ የተጠለሉ ያነጋገርናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠይቀዋል።
የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪው ቄስ ኃይሌ ሞገስ እንዳሉት በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ወረዳዎች የትግራይ ክልል አጎራባች እንደመኾናቸው የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ ኾነዋል። በዚህም የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል።
አኹንም ድረስ ከእነዚህ አካባቢዎች ሕፃናት፣ አረጋውያን እና እናቶች እየተፈናቀሉ ነው፤ ለተለያዩ በሽታዎችም እየተጋለጡ መኾናቸውን ገልጸውልናል።
በወረራው ምክንያት በ2013/14 የምርት ዘመን ማምረት ባለመቻሉ ማኅበረሰቡ ተረጂ ኾኗል። ወረዳዎችን ከወዲሁ ከሽብር ቡድኑ ማጽዳት ካልተቻለ በ2014/15 የምርት ዘመን ማምረት ስለማይቻል የተፈናቃዩ እና የተረጂው ቁጥር አኹን ካለው በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነግረውናል።

መንግሥት አካባቢውን ከጠላት ነጻ በማድረግ ነዋሪውን ወደ ቀደመ ኑሮው እንዲመልስም ጠይቀዋል።
ሌላኛው የአበርገሌ ነዋሪ አቶ እነተ ሚሰው የዋግ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲያርሱ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች በቀጣዩ የዘር ወቅት ወደ አካባቢው ተመልሶ ማምረት ካልቻለ አኹንም ዳግም ችግር ላይ ሊወድቁ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የጻግብጅ ወረዳ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳዊት ምትኩ የወረዳው ሕዝብ በሽብር ቡድኑ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ የተፈጸመበትን ትንኮሳ ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት መከላከሉን አንስተዋል። የጸጥታ ኀይሉ ብሔረሰብ አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ ነጻ ሳያወጣ ባለበት እንዲቆም መደረጉ ማኅበረሰቡን ለስደት ዳርጓል ብለዋል፡፡ መሰደድ ያልቻለው ማኅበረሰብም በሽብር ቡድኑ መዘረፉን አንስተዋል።

በጠላት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ አጎራባች ወረዳዎችን ነጻ በማድረግ ማኅበረሰቡ ወደ ማምረት እንዲገባ ማድረግ ካልተቻለ ከፍተኛ የኾነ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ያስረዱት።
መንግሥትም ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት አካባቢውን ነጻ በማድረግ ማኅበረሰቡ ወደ ቀየው ተመልሶ የተረጋጋ ህይዎት እንዲመራ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድንም ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተመልክቷል። በዚህም ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና አረጋውያንን በአንድ መጠለያ ውስጥ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ እየኖሩ ስለመኾናቸውም አረጋግጧል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተሠራ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።
Next article“በተማሪዎች ውጤት እና መቁረጫ ነጥብ ዙሪያ አስፈላጊው ማብራሪያ እንዲሰጥ ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበናል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ