
መጋቢት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ጸሎትና ቀብር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቀረበች።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ጸሎትና ቀብር የቤተክርስቲያኗ ቀኖና በተከተለ፤ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተለያዩ መንፈሳዊ መርኃ ግብሮች በሰላም መፈጸሙን ገልጸዋል።
ቅድስት ቤተክርስቲያን መላ ዘመናቸውን ሲያገለግሉ የኖሩ አገልጋዮቿን በክብር መሸኘት የዘወትር ተግባሯ ነው ያሉት ዋና ጸሓፊው፥ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከአገልጋዮቿ መካከል ቅድሚያውን የሚወስዱ ቅዱስ አባታችን ናቸው” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ቅድስት ቤተክርስቲያንን በሙያቸውና በሥልጣናቸው ከማገልገላቸውም በላይ በቤተክርቲያኗ ታሪክ በአርምሞ ኾነው በጸሎታቸው ያገለገሏት የመጀመሪያው ፓትርያርክ እንደነበሩ አቡነ ዮሴፍ ጠቅሰዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ ቤተክርስቲያኗ ድንጋጤ ላይ ብትወድቅም ሥርዐተ ጸሎቱና ሥርዐተ ቀብራቸው የቤተክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ በሰላም ተፈጽሟል።
ከዕለተ ረፍታቸው እስከ ቀብራቸው ፍጻሜ ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሐዘን ተካፋይ የነበሩትን ኹሉ አመስግነዋል።
በተለይም ብፁዕነታቸው ከ26 ዓመታት በኋላ ወደሚወዷት ሀገራቸው ተመልሰው ሽኝታቸው ባማረ ሁኔታ እንዲፈፀም ላደረጉት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ለብፁዕን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ሲኖዶሱን አንድ ለማድረግ ለደከሙ ኹሉ ቤተክርስቲያን ምሥጋናዋን አቅርባለች ብለዋል።
የቅዱስነታቸው ሥርዐተ ጸሎትና ሥርዐተ ቀብር በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም ያደረጉትን የፌደራልና የአዲስ አበባ የመንግሥት አስተዳደር አካላት፣ የፀጥታ ተቋማት፣ የሚዲያ እና ሌሎችንም ተቋማት አመሥግነዋል።
አቡነ ዮሴፍ በመግለጫቸው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ጸሎት የቤተክርስቲያንን ክብር አስጠብቆና የኢትዮጵያን ገፅታ አስውቦ እንዲፈጸም ያደረጉትን የአዲስአበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምዕመናንን በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም ማመስገናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት አባቶች፣ የእህት ቤተክርስቲያን ተወካዮች እንዲሁም በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት መጋቢት 4/2014 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መፈጸሙ ይታወሳል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J