
መጋቢት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ በነበራቸው ቆይታ ካነሷቸዉ ነጥቦች መካከል አንዱ ፋኖን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ስለሚናፈሰው ጉዳይ ነው፡፡
ኮሚሽነሩ “ፋኖ በችግር ወቅት ለነጻነቱ የሚፋለም፤ በሰላም ወቅት ደግሞ በተለያዩ ተግባራት ተሰማርቶ ለለውጥ የሚተጋ መርህን የሚከተል ነው” ብለዋል፡፡ ይህ እንዳለ ኾኖ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር አማራጮች ፋኖን ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር ለማላተም ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከሚነዙ ውዥንብሮች መካከል አንደኛዉ መንግሥት ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት እየሠራ ነዉ የሚባለዉ ሲኾን ይሄ ፈጽሞ ሥህተት መሆኑን ተናግረዋል ኮሚሽነሩ፡፡ “ይሄ አጀንዳ ከየት እንደመጣ አላውቅም የክልሉ መንግሥትም ይሁን ፖሊስ ኮሚሽን እንደዚህ አይነት እቅድ የለዉም” ብለዋል፡፡ በበሬ ወለደ አጀንዳ እየሰጡ የሕዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
“ከፋኖ አባላትና አመራሮች ጋር የጋራ ውይይት አድርገናል፡፡ በዚያ ዉይይት ላይ የተግባባነው በፋኖ ስም የሚነግዱ በተለያዩ መንገዶች ሕገወጥ ተግባራትን የሚያከናወኑ መኖራቸዉን ተግባብተናል” ብለዋል ኮሚሽነር ተኮላ፡፡ እነኝህን ሕገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ አካላትን ሕጋዊ በኾነ መንገድ ከድርጊታቸዉ እንዲታቀቡ ከጸጥታ ኀይሉና ከፋኖ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሕግ ጥላ ስር የዋሉ ታራሚዎችን በሕገወጥ መንገድ ለማስለቀቅ የተደረገ ጥረት እንደነበርና የመንግሥት ንብረት ላይ ዘረፋ እንደተፈጸመም ተናግረዋል፡፡ “ይህንን ድርጊት ትክክለኛ ፋኖ አላደረገውም፤ ነገር ግን በስሙ የሚነግዱ ሕገወጦች በዚህ መንገድ ጥፋት እየፈፀሙ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
መንግሥት ፋኖን ትጥቁን ለማስፈታት እየሠራ ነው ከሚባለው የሐሰት ወሬ በተቃራኒ የአማራ ክልል መንግሥትና ፖሊስ ኮሚሽን በኅልውና ዘመቻው ወቅት የጎላ አበርክቶ ለነበራቸዉ የፀጥታ ኀይሎች ፋኖን ጨምሮ የቡድንም ይሁን የተናጠል እውቅና ይሰጣቸዋል ሲሉ ኮሚሽነሩ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ የሰላም መደፍረሶችን በማስቀረት ሕዝቡ የቀደመ ሰላሙን ሙሉ በሙሉ እንዲቀዳጅ ኹሉም የጸጥታ ኀይል በቅንጅት እንዲሠራ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ:- ኤልያስ ፈጠነ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/