ʺበእነርሱ መደሰት በእነርሱ ፈገግታ፣ ይታየኛል ተስፋ፣ ይታየኛል ደስታ”

350

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም የሌለውን ይዛለች፣ ሌሎች የሚናፍቁትን ታቅፋለች፣ ዓለማት ሁሉ ይቀኑባታል፣ አንድም በመንፈሳዊ ቅናት፣ ሌላም በመጥላት፣ ይህችስ ባልኖረች በማለት፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ፍቅር፣ ምድርን ያጸናት ምስጢር በእርሷ ውስጥ አለ፡፡ ለምድር የተሰጡት በረከቶች በእርሷ ላይ ናቸው፡፡ ምድርን የሚጠብቁ ቅዱሳን ዓይኖች እርሷን ያያሉ፣ ምድርን የሚጠብቋት ከእሳት የላቁ ሰይፎች እርሷን ይከልላሉ፣ መልካም ነገር የሚሰሙ ጀሮዎች እርሷን ያዳምጣሉ፣ ምስጢር የሚፈልጉ እግሮች ወደ እርሷ ይገዟሉ፣ ደስታን የሚሹ ወደ እርሷ ያቀናሉ፡፡ የማያንቀላፉ ጀግኖች በተጠንቀቅ እርሷን ይጠብቃሉ፡፡
የተባረኩ አፍላጋት መፍለቂያ፣ የተጨነቁት መጠለያ፣ የበረከት ማደሪያ፣ የቅዱሳን መኖሪያ፣ አበው የሚወዷት፣ ሳይታክቱ ስሟን የሚጠሯት፣ ከምድር ወደ ሰማይ ምልጃና ጸሎት የሚያቀርቡባት ድንቅ ምድር፡፡ ቀደምን ያሉትን ሁሉ የምትቀድማቸው፣ በለጥን ያሉትን ሁሉ የምትበልጣቸው፣ ከፍ አልን ያሉትን ሁሉ ከፍ የምትልባቸው፣ በታሪክ ደመቅን ያሉትን ሁሉ ላቅ ብላ የምትደምቅባቸው፣ እኛ ጀግኖች ነን የሚሉትን ሁሉ እልፍ ጀግና ወልዳ የምታሳያቸው፣ እኛ አንሸነፍም የሚሉትን በታሪኳ ተሸንፋ እንደማታውቅ የምትነግራቸው፣ እኛ ጠቢባን ነን ለሚሉት ጥበብ ከእኔ ጉያ ነው የፈለቀው የምትላቸው፣ የጥበባትን መፍለቂያዎችም የምታሳያቸው፣ እኛ ዓለማትን አስሰናል ለሚሏት ከዘመናት በፊት ያሰሰቻቸውን ዓለማት የምትነገርቻው፣ ዛሬ እነርሱ የደረሱበትን እርሷ ከዘመናት በፊት እንደረሰችባቸው፣ብዙ ዘመናትን እንደቀደመቻቸው የምታስረዳቸው፣ እኛ ሊቆች ነን ለሚሉት የእናንተ አስተማሪዎች ሊቅነትን የሚሰጡት፣ አስቀድመው ሊቅ የሆኑት የእኔ ልጆች ናቸው የምትላቸው ድንቋ ምድር ኢትዮጵያ፡፡
ዝም ብለህ ተመልከታት፣ የተለየች፣ የተከበረቸ፣ ረቂቅ እንደሆነች ይገባሃል፡፡ በአንድ በኩል ብቻ አትመልከታት፣ በእልፍ በኩል ተዟዙረህ ተመልከታት፡፡ ያን ጊዜ በኢትዮጵያዊነትህ ትኮራለህ፣ በክብሯ ትከብራለህ፡፡ መከራዎች በበዙበት፣ ጠላቶች በተነሱበት፣ ሀገር አፍራሾች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሁሉንም አሸንፋ መምጣቷን፣ ለአሸናፊነት ብቻ መፈጠሯን ባሰብክ ቁጥር ድንቅነቷ ይገርምሃል፡፡
በእሴት፣ በሃይማኖት፣ በጸሎት፣ በአንድነት የጸናች፣ የበረታች፣ እልፍ የክፋት በትሮችን የሰበረች መሆኗን ልብ በል፡፡ እርሷን ያጸናት እሴት፣ እርሷን ያጸናት ሃይማኖት፣ እርሷን ያጸናት አንድነት፣ እርሷን ያጸናት ጀግንነት፣ እርሷን ያጸናት አትንኩኝ ባይነት፣ እርሷን ያጸናት አርቆ አሳቢነት መሆኑን አስብ፡፡ ጥቂቶች በሚያጠፉት አትዘንባት፣ ተስፋም አትቁረጥባት፡፡ እርሷ የተስፋ ምድር ኾና ሳለች ተስፋ የሚቆረጥባት፣ እርሷ የፍቅር ሀገር ኾና ሳለች ፍቅር የሚታጣባት፣ እርሷ የአዛኝነት ሀገር ኾና ሳለ አዛኝነት የሚታጣባት፣ እርሷ ስለ ሰላም የሚጸልዩ አባቶች ያሉባት ሀገር ኾና ሳለች ሰላም የሚታጣባት ሀገር አይደለችምና ተስፋዋ የማይጠፋ፣ ጠባቂዋ የማያንቀላፋ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ መልካሙን እያሰብክ፣ ለመልካም ነገርም እየተባበርክ፣ መልካም ነገርም እያደረክ በተስፋና በትዕግስት ጠብቃት እንጂ ከገፊዎች ጋር አትግፋት፣ ከነቃፊዎች ጋር አትንቀፋት፣ ተስፋ ከሌላቸው ጋር ተስፋ አትቁረጥባት፡፡
መዛግብት አስቀድመው ስሟን የሚጠሯት፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ስሟን በተደጋጋሚ የሚያነሷት፣ የተጨነቁት ተስፋችን የሚሏት፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩት ብርሃን ያዩባት፣ ብርሃናችን የሚሏት፣ ተስፋ ያጡት ተስፋችን የሚሏት ታላቋ ኢትዮጵያ አጽንቶ ያቆማት ነገር ሪቂቅ ነው፡፡ አበርትቶ ያኖራት ኢትዮጵያዊነት ምስጢር ነው፡፡
በአባትህ ፈገግታ ውስጥ ተስፋህን ፈልጋት፣ በአባትህ ሳቅ ውስጥ ደስታን ተከተላት፣ ከእርሱ ውስጥ ደስታ ከታየህ፣ በእርሱ ውስጥ ሰላም ካየህ ደስ ይበልህ፡፡ በእርሱ ፈገግታ ውስጥ ተስፋና መልካም ዘመን አለና፡፡ ሲከፋም ይክፋህ፣ በእርሱ ከፋት ውስጥ ተስፋ ሲኮሰመን፣ ሰላም ሲጠፋ ይታያልና በሐዘኑም እዘን፣ ነገር ግን ሐዘኑን ሻርለት፣ ደስታውን መልስለት እንጂ እያዘንክ ብቻ አትቀመጥ፡፡
የአንደኛው የሃይማኖት መሪ ሲሞት የሌላኛው የሃይማኖት መሪ የሚያለቅስበት፣ ጥቁር ለብሶ የሚያዝንበት፣ ሙሾ የሚያወርድበት፣ አባታችን፣ መካሪያችን፣ አዛኛችን እያለ በእንባ የሚታጠብበት ሀገር ከየት አለች ከተባለ ኢትዮጵያ ናት በል፡፡ ሰው ስትሆን የሌሎች ለቅሶ ያስለቅስሃል፣ የሌሎች ሐዘን ያሳዝንሃል፣ የሌሎች መከፋት እንቅልፍ ይነሳሃል፡፡ ሰው ስትሆን ከአለቀሱት ጋር አብረህ ታለቅሳለህ፣ ከሳቁትም ጋር አብረህ ትስቃለህ፡፡ ከደስታቸውም ከሐዘናቸውም ተካፋይ ትሆናለህ፡፡ በሳቃቸው ቀን ብቻ የምትስቅ ከሆነ ግን ስለ ሐዘናቸው የማያገባህ፣ የሌሎች መከፋት ግድ የማይሰጥህ ትባለለህ፡፡
አበው ሰውነትን አሳይተዋል፣ አበው ታላቅነታቸውን አስመስክረዋል፣ አበው ኢትዮጵያዊነትን ኖረውታል፣ መልካሙን ነገር አድርገውታል፡፡ ʺፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤
በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፣ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ ሀሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።” እንዳለ መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ከሚያለቅሱት ጋር አልቅሰዋል፣ ከሚስቁት ጋርም ስቀዋል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከድካም ማረፍ ብዙዎች አዝነዋል፣ ብዙዎች አንበተዋል፡፡ መጠለያ ዋርካ ናቸውና ዋርካችን ወደቁ፣ ጠበቂያችን ተለዩብን ሲሉ አንበተዋል፡፡ በማረፋቸው የሚያለቅሱ እርሳቸው የሚጠብቁት፣ እርሳቸው የቆሙለት፣ እርሳቸው የጸኑለት እና አክብረው የከበሩበት ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ አልነበሩም፡፡ የእርሳቸውን ሃይማኖት የማይከተሉ ነገር ግን የእርሳቸው ማለፍ እንደሚያጎድል፣ የእርሳቸው መኖር እንደሚሞላ፣ ለምድር በረከትና ረድኤት ይዞ እንደሚመጣ የሚያስቡት የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችም አንብተዋል፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ አባት ታጥተዋልና፣ ከዓላፊዋ ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ሄደዋልና አባታችን ሲሉ አልቅሰውላቸዋል፡፡
የጥበብ፣ የመልካምነት፣ የሃይማኖት አባት፣ የዘመን መብራት፣ የመልካም ነገር ምልክት፣ በጥበብ ኗሪ፣ ደግ መሪ፣ ክፉውን አሻጋሪ፣ ምስጢራትን መርማሪ፣ ረቁቁን አንጣሪ፣ ከንቱውን ዓለም የረሱ፣ በዘላለማዊ ዓለም መንገድ የገሰገሱ፣ በእውነት ተጉዘው ከእውነተኛው ዓለም የደረሱ፡፡ በከንቱ ያለፈ ሰዓት ያልነበራቸው፡፡ ለበረከት የተፈጠሩ፣ ለቅድስና በቅድስና የሠሩ፣ በቅዱስና የኖሩ አባት አልፈዋልና ሁሉም አባታችን ሲል አዘነላቸው፡፡
አበው ያዘኑትን ለማጽናናት፣ በእንባ የራሰውን ፊታቸውን በደስታ ለመተካት ፍቅራቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ በሐዘን ውስጥ ደስታ፣ በማለፍ ውስጥም ተፋስ እንዳለ አሳይተዋቸዋል፡፡ ሐዘናቸውን እንዲረሱ አይዟችሁ፣ የሁላችንም አባት ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይህ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት መተዛዝን፣ መደጋገፍ፣ የአዘነን ማጽናናት፣ የደከመን ማጽናት፣ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣት፣ ስለ ሀገር በአንድነት መውጣት ነው፡፡
ʺበእነርሱ መደሰት በእነርሱ ፈገግታ፣
ይታየኛል ተስፋ፣ ይታየኛል ደስታ” በእነርሱ ውስጥ መልካም ተስፋ ይታየኛል፣ በእነርሱ ውስጥ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ከፈገግታቸው ፍቅር፣ አንድ የሚያደርግ ምስጢር፣ ከሁሉም የላቀ የሰውነት ክብር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ ሰውነት ተመልክቻለሁና፡፡ በእነርሱ ሥር ብዙዎች ሲፋቀሩ፣ በእነርሱ ሥር ሚሊዮኖች በአንድነት ጎጆ ውስጥ ሲኖሩ ይታኛል፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላከበረና የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው” የሕግ ባለሙያ
Next articleየ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ማለፊያ ነጥብ ይፋ ኾነ።