
መጋቢት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “የኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላከበረና የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው”ሲሉ በአሜሪካ ቦስተን የሕግ ባለሙያ ደረጀ ደምሴ ገለጹ።
በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።
በአሜሪካ ቦስተን የሕግ ባለሙያ ደረጀ ደምሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት “ኤችአር 6600″ ረቂቅ ሕግ በኢኮኖሚ፣በወታደራዊ፣በሕግ አካሄድና የንግግር ይዘቶችን መገደብ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታደርግና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ብድርና እርዳታ እንዳይሰጡ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ መደበኛ የጦር መሳሪያዎችን ከነመለዋወጫዎቻቸው እንዳትገዛ ክልከላ ማድረግና መሳሪያውን የሚሸጡ ሀገራትና ባለስልጣናት በሕግ ተጠያቂ መኾን እንዳለባቸው እንደሚገልጽም አመልክተዋል።
ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ለሕግ ካልቀረቡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከሌሎች ሀገራት የምታገኛቸው እርዳታዎችና ድጋፎች መቆም አለባቸው የሚል ሐሳብ መያዙን ጠቅሰዋል።
ሕጉ ከጸደቀ ከአሜሪካ ውጪ የሚኖሩና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ ሰዎች መልዕክቶቻቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይተላለፉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ረቂቅ ሕጉ በአሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከተዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች መካከል ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የማያከብር መኾኑንም ነው ያነሱት፡፡
ረቂቅ ሕጉ “በኢትዮጵያ ሰላም፣ዴሞክራሲና መረጋጋት ማምጣት” የሚል ስያሜ ያለው ቢኾንም በውስጡ የያዛቸው ሐሳቦች በተቃራኒው ኢትዮጵያን የሚጎዱ መኾናቸውን አመልክተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ዓላማ ያለው መኾኑን አመልክተዋል።
ሕጉ ከጸደቀ ለ10 ዓመት የሚያገለግል በመኾኑ በኢትዮጵያ ላይ ቀጣይነት ያለው ጫና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
‘ኤችአር 6600’ በኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር በመኾኑ ኹሉም ኢትዮጵያዊያንና የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ሊቃወሙት ይገባል ብለዋል።
ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ መንግሥት ፍላጎት ሳይኾን የተወሰኑ የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያዘጋጁት እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ተወያይቶበት ሙሉ ኮንግረሱ እንዲወያይበት መመራቱን አመልክተዋል።
ረቂቅ ሕጉን ለማጸደቅ በአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት ባሉ የሕግ ሂደቶች ውስጥ እንዲወድቅ ወይም ደካማ እንዲኾን ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የዳያስፖራ አባላት ረቂቅ ሕጉን በሚገባ ተረድተው በየአካባቢያቸው ላሉ ተመራጮች ማስረዳት፣ ደብዳቤ መጻፍና በስልክ ማነጋገር እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የዳያስፖራ ተቋማት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዱ የአሜሪካ ባለስልጣናትን እ.አ.አ በ2022 የግማሽ ዓመት ምርጫ በድምጹ መቅጣት እንደሚገባውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስረዳት በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍን አስመልክቶ ያሉ ጉዳዮች ላይ ለአሜሪካ መንግሥት ማብራሪያ ቢሰጥ የረቂቅ ሕጉን የመጽደቅ እድል እንደሚያጠበውም ተናግረዋል።
መንግሥት ሰላምን ለማምጣት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችና እየገጠሙት ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ ገለጻ ማድረግ እንደሚገባውም አብራርተዋል።
የኢትዮ-አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ አሜሪካን ኢትዮጵያንስ ፐብሊክ አፊርስ ኮሚቴ፣ የ“በቃ” ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴና ሌሎች የሲቪክ ተቋማት የ ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ዘመቻ እያደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/