ከሢመት እስከ ስደት፣ ከስደት እስከ ሚጠት…

242

መጋቢት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም ለነብያት አትመችም፡፡ ንጉሥም በሀገሩ አይከበርም፡፡ እግዚአብሔርን በመምሰል የኖረ ኹሉ ይሳደዳል እንዳለ ቅዱስ መጽሐፍ፡፡ ክርስቲያኖችን በማሳደድ ክርስትናን ማጥፋት የሚቻል የመሰላቸው ከዲዮቅሊጢያኖስ ያልተማሩ የዲያቢሎስ አበጋዞች ቤተ ክርስቲያኗን ከጉልላቷ ለመናድ መዶሻቸውን አነሱ፡፡ ይህ የመከራው ዘመን ጅማሮ እንጂ ፍጻሜ እንዳልነበር ግን ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ያውቁ ኖሯል፡፡

ስለሃይማኖታቸው ሲሉ ሆድ ማስባስ ያልተሳናቸው አቡን ስለሀገራቸው እና ስለምዕመኖቻቸው ሰላም ሲሉ የመከራውን ዘመን ለማሻገር ራሳቸውን ገዙ፤ ዝምታን መረጡ፡፡

የክርስቶስን መስቀል ተሸክመው እንደቀደሙት ክርስቲያን ወገኖቻቸው መሳደድን በትህትና፣ በፍቅር እና በይቅርባይነት መቀበልን መረጡ፡፡

ማዕበሉን በመስቀላቸው እና ወጀቡን በበትረ ሙሴያቸው እየከፈሉ የተስፋዋን ምድር በተስፋ ለቀው ተሻገሩ፡፡ የደቀመዛሙርትነታቸው ዘመን ትጉህ ብላቴና በጎልማሳነታቸው ዘመን የተሸከሙት የክርስቶስ መስቀል እና የተቀበሉት የክርስቶስ ስልጣን እንዲታበዩ አላደረጋቸውም፡፡

በወልድ ሥም ውሉድ የኾኑት ፓትርያርኩ በክርስቶስ ክርስቲያን፤ በመንፈስ ቅዱስም የእውነት መንፈሳዊ አባት ነበሩና ሲገፏቸው ስጥና፣ ሲያስለቅቋቸው ኤሴቅ ሲያሳድዷቸውም ሮኆቦት ማለት አልከበዳቸውም ነበር፡፡

ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም አሳዳጆቻቸውን አልከሰሱም፣ አልወቀሱም፣ አልነቀሱም፡፡ ይልቁንም ስላሳደዷቸው ይቅር አሏቸው፣ ስለበደሏቸው በፍቅር አቀፏቸው፣ ስለተናገሯቸው አርምሞን መረጡ እንጂ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ትተዳደር ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊያኑም ይህን የቆየ አሠራር ቀይረው ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ፓትርያርክ የምትተዳደርበትን ሥርዐት ለማንበር ብዙ ሃይማኖታዊ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡

በ1943 ዓ.ም አቡነ ቄርሎስ 5ኛ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ ኾኑ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ናቸው ሲባል በዚህ ቅደም ተከተል ሲቆጠር ነበር፡፡ ሳሙኤል ዳዊትን፣ ሳዶቅ እና ናታን ሰሎሞንን እንደቀቡት እንደ ቀደመው ሥርዐት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም እንዲህ ተቀብተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ኾኑ፡፡

“እግዚአብሔር በሥራው አይሳሳትም” እንዲሉ ክርስቲያኖች ለኢትዮጵያ የመከራ ዘመን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በፓትርያርክነት ቀባላቸው፡፡ የፓትርያርክነት ዘመናቸው በመከራ፣ በፈተና እና በግዞት ያሳለፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከህሊና ባርነት አርነት ይወጡ ዘንድ መንበራቸውን እና ሀገራቸውን ለቀው ለ26 ዓመታት በውጭ ይኖሩ ዘንድ ተገደዱ፡፡ ስለበደሏቸው ይቅር እያሉ፣ ስለሀገራቸው እየለመኑ እና ስለምዕመኖቻቸው ሰላም እየማለዱ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በጽናት ዘለቁ፡፡

“እግዚአብሔርም ጊዜ አለው” እንዲል መጽሐፍ የመዳን ቀን ቀርቦ እና የፓትርያርኩ ልመና ደርሶ በተስፋ የተሰደዱባትን ምድር ያዩ ዘንድ ፈቃዱ ኾነ፡፡ የተስፋዋን ምድር ዳግም ረገጡ፡፡

ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መንፈሳዊ ልዕልናቸው የሚገለጸው በማሰባቸው ጥልቀት እና በአዕምሯቸው ብቃት ነበር፡፡ ነጻነት እና አዋቂነት ከተደፈቀበት መልካም ሕይዎት ይልቅ ነጻናት እና አዋቂነት ያለበትን መከራ እና ስደት መርጠው ተሰደዱ፡፡

ከስደት መልስም ስላለፈው ቀርቶ ስለሚመጣው እና እየኾነ ስላለው እንኳን ሳይናገሩ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡ ለዚህ መታደል ብቻውን በቂ አይደለም መመረጥን እና ጽናትንም ይጠይቃል እንጂ፡፡

በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleአየር መንገዱ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት ወደ ባሕር ዳር የሚደረግ በረራ መሰረዙን ገለጸ።
Next articleየብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ፡፡