አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል በወረራ ይዟቸው በነበሩ ቦታዎች የአዕምሮ ሕሙማንን ሳይቀር መግደሉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።

98

መጋቢት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአፋርና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ ባለ 110 ገጽ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

የአሸባሪው ትህነግ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳት እንዳደረሱ የኢሰመኮ ሪፖርት አጋልጧል፡፡

አሸባሪው ቡድን አባላት ‹‹በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የኾነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕጻናት፣ አረጋዊያን ሴቶች ላይ አድርሰዋል›› ብሏል ሪፖርቱ፡፡

ይህ የተፈጸመው ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃት የተጎጂዎችን እና የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ ክብር ለመጉዳት እና ለማዋረድ፣ በአብዛኛው በሴቶች ላይ በሙሉ ያለ ልዩነት፣ አልፎ አልፎም አጥቂዎቹ ኾነ ብለው ለጥቃቱ ዒላማነት በመረጧቸው ሴቶች ላይ ኾነ ተብሎ ታቅዶ በግፍና በጭካኔ፣ በግልጽ የበቀል ስሜት፣ በቡድን አስገድዶ በመድፈር፣ ድርጊቱን ኾነ ተብሎ በቤተሰብ ፊት በመፈጸም ጥቃቱን ለጦርነት ዓላማ ማስፈጸሚያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡

እነዚህ ታጣቂዎች የሕዝቡን ሞራል ለመስበርና ለመበቀል በማሰብ በሴቶች ማህፀን ላይ በዓድ ነገር በመክተት ጭምር ጉዳት በማድረስና በማሰቃየት ከሰብዓዊነት የወረደ በደል መፈጸማቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት አስረድቷል፡፡

በአውሬነት መንፈስ የአሸባሪው ቡድን አባላት በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በኾነ መንገድ ለጦርነት ዓላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ መሆኑም ታውቋል፡፡

የአሸባሪው ቡድን አባላት ‹‹ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊኾን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን የፈጸሙ ሲኾን በተለይ የአዕምሮ ሕሙማን ሳይቀሩ በትህነግ ኃይሎች የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል›› ብሏል ሪፖርቱ፡፡

እነዚህ የአዕምሮ ሕሙማን የትህነግ ኃይሎች ወደ ተቆጣጠሯቸው ከተሞች ሲገቡ ‹‹በመንገድ ላይ በመገኘታቸው፣ ወይም መንቀሳቀስ በተከለከለባቸው ሰዓታት ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው፣ ወይም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ባለመቻላቸው ወይም ለሚጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ባለመቻላቸው፣ …›› በአሸባሪው ቡድን ተገድለዋል ነው ያለው ጥናቱ፡፡

ከሰብዓዊ ጥቃቶች በተጨማሪም በሰዎች ሀብትና ንብረት፣ በሕዝብና መንግሥት ተቋማት ላይ በእነዚህ ኃይሎች የደረሰውን ውድመትና ዝርፊያ ሪፖርቱ አካቷል፡፡

ይህ የምርመራ ሪፖርትም በጦርነቱ ተሳትፈው በሲቪል ሰዎች ላይ በደል የፈጸሙ ሰዎችንና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የሚያግዝ መሆኑ የተገለጸ ሲኾን ተጎጂዎች ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ወደፊት ተመሳሳይ ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ለማስቻል ይረዳል ብሏል ኢሰመኮ።

ኮሚሽኑ በዚህ የምርመራ ሂደት በአጠቃላይ 427 ሚስጥራዊ ቃለ መጠይቆችን፣ ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ጋር 136 ስብሰባዎችን እና ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 12 የቡድን ውይይቶችን ያደረገ ሲኾን፤ ይህም ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የየአካባቢው ነዋሪዎችንና የዓይን ምሰክሮችን፣ የሆስፒታልና ጤና ባለሙያዎችን፣ የእርዳታ ድርጅቶችንና፣ ሲቪል ማኅበራትን እንደሚጨምር አሳውቋል፡፡

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለእኔም የመንፈስና የጸሎት አባቴ ነበሩ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
Next articleአየር መንገዱ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት ወደ ባሕር ዳር የሚደረግ በረራ መሰረዙን ገለጸ።