“መሪዎች የሕዝብን ሮሮ ማስታገስ የሚያስችሉ አሠራሮችን ሊቀይሱ ይገባል”

102

መጋቢት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ምሬት ውስጥ የከተተው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ሰሞነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡

በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግሥት የአደጋ ስጋት አመራር አማካሪና የምጣኔ ሀብት መምሕሩ ጉቱ ቴሶ (ዶ.ር) የምጣኔ ሀብታዊ ስብራቱ መንስዔዎች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የመፍትሔ አማራጮች አስመልቶ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዶክተር ጉቱ ለኑሮ ውድነቱ በመንስዔነት ካነሷቸው መካከል የወጪ እና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን አንዱ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ከውጪ ታስገባለች፤ በአንጻሩ ወደ ውጪ የምትልከው የምርት መጠን አነስተኛ ነው፡፡ ከፍተኛ ጭማሬ ካሳየው የዶላር ምንዛሬ ጋር ተዳምሮ ችግሩን እያባባሰው ይገኛል ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንዳሉት የነዳጅ ዋጋ መናር፣ ለተከታታይ ዓመታት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እየቀነሰ መሄድ፣ የግብርና ዘርፉ ፈተና ውስጥ መውደቁ፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የምርት እጥረቱ እንዳለ ኾኖ ያለውን ማሰራጨት የሚያስችል ጤነኛ የንግድ ሰንሰለት አለመኖር የችግሩ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ የታየው የበርሃ አንበጣ መንጋ ወረራ፣ ድርቅ እና የኮሮናቫይረስ ክስተትም ለዋጋ ንረቱ የሚነሱ ምጣኔ ኃብታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በየአቅጣጫው በሚስተዋል የሰላም እጦት ምክንያት በምርት፣ በሥርጭትና በኢንቨስመንት እንቅስቃሴ ላይ ያጋጠመው ተግዳሮትም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላም ተናግቷል፡፡ ካንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አዳጋች ኾኗል፡፡ ባለሀብቶች እምነት ኖሯቸው መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ አልቻሉም፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ስላልቻሉ ማምረት እና ማሠራጨት አዳጋች ኾኗል፡፡

ዶክተር ጉቱ እንዳሉት ምጣኔ ሀብቱን ማሻሻል ካስፈለገ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ተቋማት ሊነጣጠሉ ይገባል፤ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረው የዓለም የገበያ ዋጋ ንረትም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ከውጪ ሀገራት ኢኮኖሚ ጋር የተሳሰረ ባለመኾኑ ተጽዕኖው በዚህ ደረጃ ሊሆን አይገባውም ባይ ናቸው፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በሰጡት የመፍትሔ ሐሳብ ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ የምጣኔ ሀብት አቅሟ እስከምትመለስ የውጪ ምንዛሬ ተመኑን ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ምጣኔ ሀብታዊ ርምጃዎች መካከል እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ ይህም በመንግሥት የአንድ ቀን ውሳኔ በጥቂቱም ቢሆን የገበያ መረጋጋት መፍጠር እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡ አንገብጋቢ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር እና ለወሳኝ የፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ዋንኛው መፍትሔ ሲኾን የውስጥ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ባለሀብቱ ወደሥራ እንዲገባ ማበረታታት ደግሞ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ምርት በተሳለጠ መልኩ የሚሰራጭበትን ሰንሰለት መፍጠርም የመፍትሔው አካል ነው፡፡

ኹሉም በፖለቲካ፣ በብሔር እና በሃይማኖት ከመናቆር ወጥቶ ተስፋ የሚሰጥ እና የነገዋን ኢትዮጵያ በጽኑ ዓለት ላይ የሚያቆም ምጣኔ ሀብታዊ አጀንዳ ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡

የብዙኀን መገናኛ ድርጅቶች ጉዳዩን አስመልክቶ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሥራ መሥራት ይገባቸዋል ያሉት ዶክተር ጉቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም መንገዱን ማሳዬት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ምሁራንም ስለ ምጣኔ ሀብት በስፋት የሚመክሩበትን መድረክ ሊያመቻቹ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይ ነጋዴው በአቋራጭ ለመክበር ከሚሯሯጥ ሕዝብና ሀገርን ሊያሻግር የሚችል ጤናማ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ መሪዎች የሕዝብን ሮሮ ማስታገስ የሚያስችሉ አሠራሮችን ሊቀይሱ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ ከኾነ የኢትዮጵያን ችግር በተወሰነ መልኩም ቢኾን መፍታት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleዜና መጽሔት ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
Next article“በሀገር ግንባታው ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች እና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው” ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ