‹‹ወቅታዊውን የዋግ ሕዝብ የከፋ ችግር መመልከት እና ምላሽ መስጠት ከኢትዮጵያዊነት በላይ ሰብዓዊነትም ነው!››

359

የካቲት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዋግ ሹምን ከስሃላ እስከ ድሃና፤ ከዝቋላ አስከ ጋዝጊብላ፤ ከአበርገሌ እስከ ፃግብጂ፤ ከወፍላ እስከ ከኮረም፤ ከዛታ እስከ ሰቆጣ ዙሪያ ገባውን አይቻዋለሁ፡፡

በዋግ ምድር እግሩ የረገጠ ሁሉ ‹ያለምወ! የምወድህ!› እየተባለ እንኳን ደህና መጣህ ይባላል እንጅ ከቶውንም ከየት መጣህ? የሚታወሰም፤ የሚታወቅም አይደለም፡፡

በመከራ እና በፈተናም ውስጥ ኾኖ እንኳ ስለሌሎች አብዝቶ የመጨነቅ ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊነት ውልደቱ እና እድገቱ ዋግ ምድር ይመስላል፡፡

ዋግ የተፈጥሮ ሀሩር ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ አረርም የለበለባት የተስፋ ምድር ናት፡፡ የሀገርን መከራ ተሸክማ ሀገር ያተረፈች የሀገር ምሰሶ እና የትውልድ ባለውለታ ናት፡፡

ዋግ ሹም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት የአብራክ ክፋይ ልጆቹን ያለስስት ገብሮ በደሙና በአጥንቱ ሀገር ያቆመ ባለውለታ ሕዝብ ነው፡፡

በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ኢትዮጵያ የነበረችበትን የታሪክ ከፍታ እና የእነ ጄነራል ኃይሉ ከበደን ለነፃነት የከፈሉትን ተጋድሎ እንዲሁም ከ1960ዎቹ የፖለቲካ ትግል ጀምረን ታሪካችን እና የመጣንበትን መንገድ ብንመረምር እንኳ የዋግ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊነት የከፈለውን መስዋእትነት ኹሌም የሚዘከር ነው፡፡

ዛሬ እስከ… ተብሎ ለሚቆጠረው እና በየአካባቢው ለተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ ነጻነት መሰረቱ የዋግ ምድር እና ሕዝብ ነው፡፡

ካመነ የማይከዳው እና ንዋይ ሰብዓዊነቱን የማይነጥቀው የዋግ ሕዝብ ያለውን ሳይሰስት የሚሰጥ ነው።

በሥልጣን ዘመናቸው ነጻነት አልባ የኾኑት ነጻ አውጭዎች ከደርግ ጋር በነበራቸው የትጥቅ ትግል መደበቂያ ጓዳቸው እና መሸሸጊያ ዋሻቸው የዋግ ምድር ነበር፡፡

የዋግ ሕዝብ ‹‹ዓሳውን ለማግኘት ባሕሩን ማድረቅ›› ተብሎ የደርግ በትር ክፉኛ አርፎበታል፡፡ ያንን መከራ እና ስቃይ ችሎ ኢትዮጵያዊነትን ታድጓል፡፡ የዋግ እናት እርጎ እና ወተቱን እንተወውና መቀነቷን ገመድ አድርጋ ስንት ኪሎ ሜትር አቆራርጣ በጠራራ ፀሐይ ውኃ ቀድታ ታጋዮችን ውኃ አጠጥታለች፡፡ የዋግ አባት ልጁን ከመገበር አልፎ ከተፈጥሮ እና ከጠላት ጋር ግብ ግብ እየገጠመ ማረሻ ጨብጦ እርፍ አገላብጦ ያመረተውን ምርት ለነጻ አውጪዎች ምግብ ያለስስት የለገሰ ታታሪ እና ደግ ሕዝብ ነው፡፡

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያቆረቁዝ የነበረው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ትከሻ ሲሽቀነጠር ከማንም በላይ ዳፋው ያረፈው በዋግ ሕዝብ ላይ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚበረታበት ያ! የየዋሆች ምድር ከተፈጥሯዊ ፈተና በላይ የሽብር ቡድኑ ፈተና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ኾኖበት ዘልቋል፡፡

ሕዝቡ በወቅቱ አርሶ ችግሩን እንዳይቋቋም አካባቢው ከስድስት ወራት በላይ በሽብር ቡድኑ ወረራ እንዳልነበር ኾኗል፡፡

በሽብር ቡድኑ ወረራ የዋግ ሕዝብ ወርቃማ ጊዜውን ተነጥቋል፣ ሰብዓዊነቱ ተጎሳቁሏል እንዲሁም ጥሪቱ አንድም ሳይቀር ተዘርፏል፡፡

ያለውን ተካፍሎ መብላት ከእምነቱ በላይ እሴቱ ለሆነው ሕዝብ ዛሬ ላይ ‹‹እንኳን መብላት ማብላት ይቀራል›› እያለ እንዲያዝን እና እንዲቆዝም ተገድዷል፡፡

በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የበዛ መከራ እና በደል በሌሊት ሲጓዝ አድሮ በጠዋት ሰቆጣ ለሚገባው በሽህ ለሚቆጠር ተፈናቃይ ነገሮች የሞት ሽረት ትግል እየኾኑበት ይመስላል፡፡ በየቀኑ ወደ ሰቆጣ የሚመጣው የተፈናቃይ ቁጥር ከ52 ሺህ በላይ ደርሷል ያሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኅላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ናቸው፡፡

በአካባቢው የገጠመው ወቅታዊ ችግር ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች አሉት የሚሉት ኅላፊው ተፈጥሯዊ ችግሩ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አራት ቆላማ ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ ነው፡፡ ሰው ሠራሽ ችግሩ ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት አካባቢውን በወረራ በያዘበት ወቅት የሕዝቡን ሃብት እና ንብረት ሙሉ በሙሉ መዝረፉ እና አሁንም ድረስ ነጻ ባልወጡ አካባቢዎች የሚሰደደው ሕዝብ በየቀኑ መጨመሩ ነው ይላሉ፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ አራት ወረዳዎች ተፈጥሯዊ ድርቅ ተከስቷል ያሉት አቶ ከፍያለው ስሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች በድርቁ ምክንያት አፋጣኝ ድጋፍ ይሻሉ ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በአካባቢዎቹ በወረራ በቆየባቸው ወራቶች የሕዝቡን ሃብት እና ንብረት በመዝረፉ ችግሩ ካለፉት ጊዜያት የከፋ ነውም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁንም በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር ያሉት የወፍላ፣ ኮረም፣ አበርገሌ እና ጻግብጂ አካባቢ ዜጎች የሚደርስባቸውን መከራ በመፍራት በየቀኑ ወደ ሰቆጣ ከተማ እየተፈናቀሉ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደመጣ የነገሩን መምሪያ ኅላፊው ችግሩ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ እና ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ እየኾነ ነው ብለዋል፡፡ ከወትሮው በአካባቢው የማይጠፉት የእርዳታ እና የሰብዓዊ ድርጅቶች ‹‹በአካባቢው የጸጥታ እና የደኅንነት ችግር አለ›› በሚል ሰበብ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ፈቃደኛ አለመኾናቸውንም ነው አቶ ከፍያለው የገለጹት፡፡

በአካባቢው የከፋ የምግብ እና የጤና ችግር እንደተከሰተ የነገሩን የኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኅላፊው ችግሩ አስቸኳይ የኾነ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገዋልም ብለዋል፡፡ ለተፈናቃዮች እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እና የጤና ቁሳቁስ ማቅረብ ጊዜ የማይሰጠው ጊዜያዊ መፍትሔ እንደኾነ ነው አቶ ከፍያለው የሚናገሩት፡፡ ለዚህም በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ዞኖች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስቸኳይ የድጋፍ እጆቻቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአካባቢው የተፈጠረው ወቅታዊ የኅልውና ፈተና በዘላቂነት የሚፈታው ደግሞ መንግሥት በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ሥር ያሉ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ ነጻ ሲያደርግ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ነው ያሉት አቶ ከፍያለው የፌደራል መንግሥት ፊቱን ወደ ዋግ እና አካባቢው ሊያዞር ይገባል ብለዋል፡፡

ዜጎች ለከፋ ሰብዓዊ ችግር ተጋልጠዋል ያሉት ኅላፊው አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው ግን በቅርቡ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ እንደሚኾን ነው ያመለከቱት፡፡ ሌላው ቢቀር መንግሥት፣ ሰብዓዊ ድርጅቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅታዊውን የዋግ ሕዝብ ችግር መጎብኘት እና መመልከት ይገባዋል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

እኛም ‹‹ወቅታዊውን የዋግ ሕዝብ የከፋ ችግር መመልከት እና ምላሽ መስጠት ከኢትዮጵያዊነት በላይ ሰብዓዊነትም ነው›› እንላለን፡፡ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርግ የሰሜን ሸዋ ዞን ጠየቀ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ-እስራኤል ፓርላማ ወዳጅነት ሕብረት ለኢትዮጵያ ስለሚደረግ ድጋፍ ምክክር አደረገ፡፡