ʺየራያ አላማጣና የአካባቢው ሰቆቃዎች”

226

ባሕር ዳር: የካቲት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባለ እርስቶች ስደተኞች፣ ባለፀጎች የሰው እጅ ጠብቀው አዳሪዎች፣ ማርና ወተት አጠጪዎች ውኃ ለምነው ጠጪዎች ኾነዋል፡፡ ነጻ ኾነው ተወልደው፣ ነጻ የኾነ ማንነት እያላቸው ነጻነታቸውን የሽብር ቡድኑ ቀማቸው፣ ደጎች፣ ለተራበ አጉራሾች፣ ለተጠማ አጠጪዎች፣ ለታረዘ አልባሾች፣ ያዘነን አጽናኚዎች ዘመንና ዘመነኛ ገፍቷቸው፣ በደል በዝቶባቸው፣ ተገፍተው እንዲኖሩ ተገደዱ፡፡

የራያ ጀግኖች የተቀሙትን ማንነት ለማስመለስ በረሃ ከወረዱ ዓመታት ተቆጥረዋል፣ መውዜራቸውን አንግተው፣ ማንነታቸው ሳይመለስ፣ ፍቅርና ሰላም እንደቀደመው በራያ ምድር ሳይታይ ላይመለሱ ቆርጠው ወጥተዋል፡፡ የራያ ወጣቶች ስለ ማንነት ሲሉ መሪር ሞትን ቀምሰዋል፣ ግንባራቸውን ለጥይት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ተዋርዶ ከመኖር ተከብሮ መሞትን መርጠው ሞትን ንቀዋል፡፡

ደጎቹ የራያ እናቶች ልጆቻቸውን አጥተዋል፣ ወገባቸውን በጥቁር ገመድ አስረው ስለልጆቻቸው፣ ስለ ጠፋች ሰላማቸው፣ ስለ ተቀሙት ማንነታቸው፣ በረሃ ስለወረዱት ባሎቻቸው፣ ስለሚታገሉት ጀግኖቻቸው አዝነዋል፣ አንብተዋል፣ በሐዘን ውስጥም ኖረዋል፡፡ ራያዎች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው፣ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ ተገድደዋል፣ እናት እና ልጅ በግፍ ተለያይተዋል፣ የራያ የሽምግልና ሥርዓት ፈጻሚ አባቶች ማንነታቸው፣ ሥርዓታቸው አንድ ሆኖ ሳለ ተለያይተው እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡

ከዓመታት በኋላ በ2013 ዓ.ም ማንነታቸውን እና ነጻነታቸውን አግኝተው የነበሩት የራያ አላማጣና ሌሎች የራያ አካባቢዎች ደስታቸውን ሳይጠግቡት ዳግም ወረራ ተፈጽሞባቸው፣ በማንነታቸው ላይ ዳግም ግፍ ተጭኖባቸው በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ግፉ እየበዛ ሲመጣና የወገን ጦር ባለበት ሢረጋ አካባቢያቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዱ፤ ሳይወዱ ቀያቸውን ጥለው የወጡ ወጣቶች እንዳሉን የራያ ወላጆች ልጆቻችሁን ለዘመቻ ስጡን እየተባሉ መከራው በዝቶባቸዋል፡፡ የገንዘብ መዋጮ እየተጣለባቸው ገንዘብ እንዲያወጡ፣ ገበሬዎች እህል እንዲሰጡና ወራሪውን እንዲመግቡ እየተገደዱ ነው፡፡

አርሰው የሚበሉት መሬታቸው በምሽግ ስም እየተቆፈረ ከእርሻ ውጭ እንዲሆኑም ተደርገዋል፡፡ የራያ ሃብት እየተጫነ ወደ ትግራይ እየተጓዘ ነው፣ በማንነቴ አትምጡብኝ የሚለው በግፍ እየተገደለ፣ እየተሳረ መከራው እንደጸናበትም ወጣቶቹ ነግረውናል፡፡

የትግራይ ክልል አርማን እና የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ አንጥፈው አንዱን ረግጠህ ውጣ እያሉ በነዋሪዎች ላይ ግፍ እንደሚፈጽሙም ተናግረዋል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያን ሠንደቅ አረግጥም ብሎ አሸባሪዎቹ አርማችን ነው የሚሉትን የረገጠ መከራው እንደሚጸናበትም አስረድተውናል፡፡ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ እየፈለጉ እንደሚያቃጥሉም ወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡ አካባቢውን የለቀቁት በስደት፣ በዚያው የሚኖሩት በግፍና በማንነት እጦት ምክንያት እየተሰቃዩ ነው፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የራያ ነዋሪዎች ለቅቀውት ከመጡት ቤት ውስጥ ከትግራይ ሰው እያመጡ እያስገቡበት መኾናቸውንም ወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡ በየቤቱ ሰው እየተለቀመ ለጦርነት እንዲዘጋጅ እየተደረገ ነው፣ ለዳግም ወረራ እየተዘጋጁ መኾናቸውንም አካባቢውን ጥለው የወጡ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡

የራያ ተዋላጆች በየቀኑ አካባቢያቸውን ለቅቀው እየተሰደዱ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በየቤቱ እየገቡ ከልጆች አፍ እየነጠቁ እንደሚመገቡና ዘረፋ እንደሚፈጽሙም እማኞቹ ይናገራሉ፡፡ በአላማጣ ከተማ በገበያና በተለያዩ ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ ወጣቶችን በግዴታ እንደሚያፍሱም በሥፍራው የነበሩት ነግረውናል፡፡ አፈናው ሲበዛ በሌሊት አካባቢያቸውን ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ነው ያስረዱን፡፡ በአላማጣና በሌሎች በወራሪው በተያዙ ከተሞች የሽብር ቡድኑን ፕሮፖጋንዳ ከሚያራግቡ ሚዲያዎች ውጭ መከታተል እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን ሃሳብ የማያራምዱ ሚዲያዎችን ሲከታተል የተገኘ ሰው እስር፣ ግርፋትና ግድያ እንደሚጠብቀው ነው የገለጹት፡፡ በተለይም የወገን ጦር እየገፋ በነበረበት ወቅት በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለውን ሂደት ለመመልከት ሌሎች ሚዲያዎችን ከፍተው የተገኙ ሰዎች
በግፍ መገደላቸውን አስታውሰዋል፡፡

የራያ ሕዝብ በጨለማ ውስጥ ነው ያለው ያሉት ወጣቶቹ መንግሥት ዘመቻውን እንዲገፋና ነጻነታቸው እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡ ከሰሞኑ ከአላማጣ ከተማ የወጡ ወጣቶች እንደሚሉት በሃይማኖት ተቋማት ላይ ስብክትና አገልግሎት በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲሆን እያስገደዱ ነው፡፡ ሕዝቡ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡ የወገን ጦር እየገፋ በነበረበት ወቅት ሕዝቡ ወገን እስኪደርስለት ድረስ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረ ቢኾንም ባለህበት እርጋ ሲባል ማዘኑንም አስታውሰዋል፡፡ ስቃዩም ከፍ እያለ ሄዷል ነው ያሉት፡፡

የወገን ጦር እያጠቃ በነበረበት ወቅት አየር ኀይል ወደ ውስጥ ገብቶ ጥቃት ያደርስ ስለነበር በአየር ኀይሉና በድሮን ለማሳበብ ሞርተር ወደ ገበያ እየተኮሱ ሲገድሉ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ሕዝቡን መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ነው የመቷችሁ ለማለት ራሳቸው በከባድ መሳሪያ ይጨፈጭፉ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ሰበብ በርካታ ንጹሐን መገደላቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጠላትን በደንብ እናውቀዋለን ያሉት ወጣቶቹ ጠላት እስኪጠፋ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ለወሳኙ ትግልም ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የራያ ወጣቶች በመደራጀት ጠላታቸውን ለማጥፋትና ማንነታቸውን ለማስመለስ እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ዝግጅታቸው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከሕዝብ ጎን ኾነው የተቸገረውን ሕዝብ ለማዳን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የራያ ስቃይ የራያ ብቻ ሳይኾን የሁሉም ሕዝብ ሊኾን እንደሚገባና ሁሉም ከራያ ሕዝብ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

የራያ ወጣቶች በጠንካራ ሥነ ልቦናና በአንድነት በመቆም ጠላታቸውን እስከመጨረሻው እንዲያጠፉም አሳስበዋል፡፡ ወጣቶቹ የጠላትን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ መኾናቸውን እና በሚኖረው ትግል ግንባር ቀደም ታጋዮች እንደሚኾኑም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/i

Previous articleግሎባል አሊያንስ ከልማት ማኅበራት ጋር በመሆን በሰቆጣ ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው።
Next articleየኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርግ የሰሜን ሸዋ ዞን ጠየቀ፡፡