
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 02/2012 ዓ/ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምትገነባቸው የባቡር መንገድ ዝርጋታዎች ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራች መሆኗን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ከአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ በሚዘረጋው የባቡር መስመር የግንባታ ሥራ በርካታ የውጭ ሀገራትና ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ አስተያዬታቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሰጡት ኢትዮጵያውያን መሃንዲሶች ፕሮጀክቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደተደረገበት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ኤሌክትሪካል መሃንዲስ ዮሴፍ በቀለ በፕሮጀክቱ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ማሰራጫዎችን እየከታተሉ እንደሆነ ገልፀው በቂ ልምድና እውቀት እንዳገኙበት ተናግረዋል። በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅታቸው ወቅት የተማሩትን ከታዋቂ ባለሙያዎች ጋር በተግባር በማየታቸውና በመስራታቸው ጥሩ ልምድ እንደቀሰሙም ነው የተናገሩት፡፡ እንደ መሃንዲሱ አስተያዬት በባቡር ኤሌክትሪካል ምህንድስና ዘርፍ ኢትዮጵያውያኑ ባገኙት ልምድና እውቀት ወደ ፊት ሀገሪቱ ለውጭ ባለሙያዎች የምታወጣውን ወጪ መቀነስ ይችላሉ፡፡
የምድር ባቡር መሃንዲስ ጥበቡ ጳውሎስ በድልድይ ሥራ፣ በሀዲድ ንጣፍና በዋሻ ውስጥ መንገዶች ትኩረት ያደረገ ሥራ እንደሚያከናውኑ፣ ፕሮጀክቱም በአውሮፓ የጥራት ደረጃ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ባለሙያዎች በቂ እውቀት እንዳገኙ ነው የተናገሩት፡፡ ከውጭ ባለሙያዎቹ ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፈ በሰዓትና በሰው ሃይል አጠቃቀም ላይ ትልቅ ትምህርት እንዳገኙ የተናገሩት መሃንዲሱ “ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታስገነባቸው የባቡር ፕሮጀክቶች እኛ በቂዎች ነን” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ፕሮጀክት የሴክሽን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻሎም አሽሮ ፕሮጄክቱ አዲስ እንደመሆኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከውጭ ሀገራት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ከቱርክ፣ ከፈረንሳይ፣ ከፖርቹጋልና ከሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት የመጡ በመሆናቸው ለሀገሪቱ መሃንዲሶች መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ለቀጣይ ሥራዎች ጥሩ እውቀት ተይዟል ያሉት ኢንጂነሩ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ከቴክኖሎጂ ጋር የመተዋወቅና ራሳቸውን የማብቃት ዕድል እንዳገኙም ነው ያስረዱት፡፡ በባቡር ፕሮጀክት ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተማሪዎች እንዳሉና በቀጣይ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣቸውን ባለሙያዎች የመተካት አቅም እየዳበረ እንደሆነም ኢንጂነር ሻሎም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እየተገነባ የሚገኘው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ወልዲያ (ሃራ ገበያ) ባቡር ፕሮጀክት 392 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝምና በ 42 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ጥቅምት 2007 ዓ.ም ግንባታው እንደተጀመረ ይታወሳል፡፡ለሥራውም 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ነው የተመደበው፡፡
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ