
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አድካሚ በሆነችው ዓለም ብርቱ ሆነው የተገኙ፤ ፈታኝ በሆነው ሕይዎት ጽናታቸው ምሳሌ የነበረ፤ ሐሰት በበዛበት ምድር እድሜ ዘመናቸውን ከእውነት ጋር የኖሩ ናቸው፡፡ ያስተማሩትን በተግባር የገለጹ፣ ትጉህ እረኛ፣ እውነተኛ ዳኛ፣ የመንፈሥ እና የሥጋ አባት ሆነው እድሜ ዘመናቸውን በጽናት አሳልፈዋል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዎስ፡፡
ብፁዕነታቸውን ዓለም እንደርሳቸው አድርጋ የፈተነችው ያለ አይመስልም፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት፣ ከጺም እስከ ሽበት፣ ከክሕነት እስከ ሊቅነት፣ ከዲቁንና እስከ ፕትርክና፣ ከምንኩስና እስከ ጵጵስና ሀገራቸውን እና ሃይማኖታቸውን በጾም በጸሎት፣ በምልጃ በስግደት በትጋት አገልግለዋል፡፡
ትግላቸው ምድራዊ ፈተናን ድል ከመንሳት አልፎ ሰማያዊ ኑባሬን እስከመጎናጸፍ ይሻገራል፡፡ አባትነታቸውን የሚወጡት የመከራን ቀንበር በልጆቻቸው ጫንቃ ላይ በማዋል ሳይሆን እርሳቸው በመሸከም ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፈተና ሁሉ ተቀብለው ስለኢትዮጵያ መከራ በተጋድሎ እድሜ ዘመናቸውን ኖረዋል፡፡
በቀደመ ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ ይባሉ ነበር፡፡ ትውልዳቸው በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ አረጊት ኪዳነ ምሕረት ልዩ ስሟ ማር ምድር ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ለምለም ገሰሰ 1930 ዓ.ም አብዝታ የፈተነቻቸውን ግን ንቀው በአርምሞ ድል ያደረጓትን ምድር ተቀላቀሉ፡፡
ስለተመረጡ ይሆናል ለትምሕርት ቆላ እና ደጋው፣ ርሃብ እና ጥሙ፣ መውጣት እና መውረዱ ሳይበግራቸው በበርካታ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው መንፈሳዊ እውቀትን እና ሀገራዊ እውነትን ቀስመዋል፡፡ በትውልድ ቀያቸው አረጊት ኪዳነ ምሕረት የተጀመረው ትምሕርታቸው መነዘጉር፣ ጎንጂ ቴዎድሮስ፣ ዋሸራ፣ አጭቃን ኪዳነ ምሕረት፣ ቤተ ልሔም እና ሌሎች አካባቢዎችን አካሏል፡፡
ብፁዕነታቸው በዘመናቸው መጨረሻ ለደረሱበት የመንፈስ እና አባታዊ ልዕልና ከመሪጌታ ላቀው እስከ መሪጌታ ወርቁ፣ ከመሪጌታ ማዕበል እስከ መሪጌታ ሙጨ፣ ከመሪጌታ ሚናስ እስከ መሪጌታ ውብ አገኝ አሻራቸውን ያሳረፉባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ንባብ እና ዳዊት፣ ቅኔ እና ዝማሬ መዋሥዕት፣ አቋቋም፣ ድጓ እና ጾመ ድጓን በልጅነታቸው ተምረዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያኽል ድጓን ያስተማሩት፡፡ ብፁዕነታቸው ሥርዓተ ምንኩስናን ከመምሕርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ እንደነበር ይነገራል፡፡
በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባትም ማዕረገ ምንኩስናን ከመምሕር ኃይለ ማርያም 1961 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡ በዚሁ ዓመትም ማዕረገ ቅስናን ከጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ይናገራል፡፡
በቀድሞ አጠራሩ በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥነ ሥርዓት እያጠኑ እና በበጎ ተግባር እያገለገሉ ለኹለት ዓመታት በገዳሙ ቆይተዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በማቅናትም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እያገለገሉ ጎን ለጎን ትርጓሜ ሐዲሳትን እና አቡሻኽርን ተምረዋል፡፡
ሲመተ ጵጵስናቸው ከጥር 13/1971 ዓ.ም ይጀምራል፡፡ በወቅቱ ቤተ ክረስቲያኗ በቅድስ ሲኖዶስ፣ በካሕናተ ቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ምርጫ 13 ኤጲስ ቆጶሳትን ስትመርጥ አንዱ ብፁዕነታቸው ነበሩ፡፡ በኦጋዴን አውራጃ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ለሐዋሪያዊ ሥራ ተሰማሩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ የኦጋዴን ቆይታቸው በኋላ ደግሞ ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተዛወሩ፡፡
በጎንደር ሀገረ ስብከት ቆይታቸውም በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፤ የደከመውን አድሰው፣ የተጓደለውን ሞልተው፣ የጎበጠውን አቃንተው አባታዊ ተልዕኳቸውን ያለመታከት ተወጥተዋል፡፡
የመንፈስ ልጆቻቸውን በእውቀት ሞልተው፣ በሃይማኖት አጽንተው እና በምግባር አደርጅተው ለትውልዱ እረኛ ይሆኑ ዘንድ አዘጋጅተዋቸዋል፡፡
የሀገሪቱ ቅርሶች እንዳይጠፉ፣ ጥንታዊ መጽሕፍት ለትውልድ እንዲደርሱ፣ የአብነት ትምሕርት ቤቶች እንዲደረጁ አባታዊ ጥረታቸው የላቀ እንደነበር ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያዊው ብርቱ ሐዋሪያ በየጊዜው በሚያሳዩት ሃይማኖታዊ ትጋት እና መልካም የሥራ ውጤት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ ለ11 ዓመታት ያክል ኤጲስ ቆጶስ እና ሊቀ ጳጳስ በመኾን በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ያገለገሉት ብፁዕነታቸው ለፓትርያርክ ምርጫው ተመዝነው ብቃትና አርአያነት ያላቸው አባት ኾነው በመገኘታቸው በእጩነት ተመረጡ፡፡
109 መራጮች በተሰባሰቡበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 22/1980 ዓ.ም ለፕትርክና ምርጫው ድምፅ ተሰጠ፡፡ በእጩነት ከቀረቡት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው ተመረጡ፡፡
ሲመተ ፓትርያርክነታቸው ነሐሴ 29/1980 ዓ.ም ተፈጽሞ አራተኛው ፓትርያርክ በመኾን ቃለ መሐላ ፈጸሙ፡፡
በፖለቲካዊ ግፊት እና ጫና መንበራቸውን እስከለቀቁበት ነሐሴ 28/1983 ዓ.ም ድረስም ለሦስት ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አባታዊ አገልግሎታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ሀገራቸውን በግፍ እንዲለቁ ከተደረጉ በኋላ ለ26 ዓመታት በአካለ ግዞት በውጭ እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡
በረከታቸው እና መንፈሳዊ አባትነታቸው ያልራቃት ሀገረ ኢትዮጵያ ዳግም ብፁዕ አባታችን ተቀብላ ወደ መንበረ ፓትርያርክነታቸው ሐምሌ 25/2010 ዓ.ም ተመለሱ፡፡
በትጋታቸው አርአያ፣ በጽናታቸው ምሳሌ፣ በሊቅነታቸው ቀዳሚ እና በአባትነታቸው የሁሉም የሆኑት ብፁዕነታቸው ትጋታቸውን በአርምሞ ከውነው ወደዚህ ዓለም እንደመጡ በሚነገርለት ዕለተ መርቆሪዎስ እረፍተ ሥጋቸውም የካቲት 25/2014 ዓ.ም በሰማዕቱ መርቆሪዎስ ሆነ፡፡
በረከትዎ በእርስተ ሀገርዎ ኢትዮጵያ ላይ ሁሉ ይሁን! ምንጭ፡- ሐመረ ኖህ
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/