ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው።

170

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

‘ኤችአር 6600’ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።

ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት መክሰስ አላማም ያለው ሲሆን የቪዛና ጉዞን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል ያስቀምጣል።

‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት እንደሚካሄድ የኒውዮርክ ኒውጀርሲ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታፈሰ ገልጸዋል።

ሰልፉ ሕጉን ባረቀቁት የኒውጀርሲ የኮንግረስ አባል ቲም ማሊኖውስኪ የሚሰሩበት ቢሮ ፊት ለፊት እንደሚከናወንና እሳቸውንና ሕጉን የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።

ሕጉን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሚቃወሙትና የኮንግረስ አባሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

“ቶም ማሊኖውስኪ ያረቀቁት ሕግ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የሚጎዳና የማይጠቅም ነው፤ ማሊኖውስኪ እየፈጸሙት ያለው መልካም ያልሆነ ተግባር በሚኖሩበት ግዛት የመረጧቸው ዜጎች እንዲያውቁት እናደርጋለን” ብለዋል አቶ አክሊሉ።

ረቂቅ ሕጉ ኤርትራንም የሚመለከት በመሆኑ በሰልፉ ላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኤርትራውያንም እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል።

በቀጣይ በአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ለማካሄድ መታሰቡን አመልክተዋል።

ረቂቅ ሕጉን የሚቃወሙ እንዲሁም በአሜሪካ ኮንግረስ ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ እንዳይሰጥበት ለማድረግ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ነው አቶ አክሊሉ የገለጹት።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያን የመረጧቸውን በየአካቢያቸው የሚገኙ የኮንግረስ አባላት በማነጋገር፣ ደብዳቤ በመጻፍና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም አሜሪካውያንና በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች ሕጉ አሸባሪውን ሕወሓትን የሚደግፍና ኢትዮጵያን የሚጎዳ መሆኑን እንዲረዱት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዳያስፖራው “አገርን ማፍረስ” ግብ ያለውን ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ረቂቅ ሕጉ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን የማስገንዘብ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ኢትዮጵያውያንም በአገር ውስጥ ሆነው የተቃውሞ ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ በመቃወም በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተስፋ ለኢትዮጵያ ከ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ)፣ ኤርትራ አሜሪካውያን ብሔራዊ ምክር ቤትና ሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል ጋር በመተባባር ያዘጋጀው እንደሆነ ተገልጿል። ዘገባው የኢዜአ ነው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“አትንኩኝ ባይ እለኸኞች፣ የበረሃ መብረቆች”
Next articleትጋት፡ ከመርቆሪዎስ እስከ መርቆሪዎስ!